የማስታወቂያዎቻችን ጉዳይ

በከተማችን የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም በከተማዋ መግቢያ እና መውጫዎች ላይ በብዛት ከሚስተዋሉ ነገሮች መካከል የሚሰቀሉ ማስታወቂያዎች ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ማስታወቂያዎች በተለያየ ይዘት እና መጠን ተዘጋጅተው ድርጅቶች እና አገልግሎቶች የሚተዋወቁባቸው ናቸው። እነዚህ ማስታወቂያዎች ድርጅት እና አገልግሎት ሰጪን ከተጠቃሚ ጋር በማገናኘቱ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ቢሆንም፤ ጐን ለጐን ግን ጥቂት የማይባሉ ጉዳቶች (እንከኖች) አሏቸው። የመጀመሪያው እንከን የከተማን ገፅታ መቀየር ነው። ማስታወቂያዎቹ እንደየባህሪያቸው የተለያየ ይዘት ያላቸው ስለሆኑ በተለያየ ቀለም እና መጠን ነው የሚቀርቡት። ይህ የተደበላለቀ ሁኔታ ደግሞ ከተማዋ ወጥ የሆነ መልክ እንዳይኖራት የማድረግ ባህሪይ አለው። ሌላው የእነዚህ ማስታወቂያዎች አሉታዊ ገፅታ ደግሞ በወቅቱ መወገድ ባለመቻላቸው የሚያስከትሉት ችግር ነው። ብዙዎቹ ማስታወቂያዎች አንድ ጊዜ ከተሰቀሉ በኋላ አስታውሶ የሚያነሳቸው አይኖርም። ለአንድ ወቅት ብቻ ታስበው የተሰቀሉ ማስታወቂያዎች ሳይቀሩ ጊዜያቸው ካለፈ በኋላ ከተሰቀሉበት ሳይወርዱ ይቆያሉ። በዚህ ቆይታው ወቅት ፀሐይና ዝናብ ስለሚፈራረቁባቸውም ወረቀቶቻቸው እና ሸራዎቻቸው የመሰነጣጠቅ፣ ብረቶቻቸውም የመነቃቀል ችግር ይፈጠራል። በዚህም ሳቢያ ለእይታ ጥሩ ካለመሆናቸውም በተጨማሪ አካባቢን የማቆሸሽ እንዲሁም እይታን የመጋረድ ሁኔታ ይፈጥራሉ።

አንድ አስተዋዋቂ ድርጅቱን ወይም አገልግሎቱን በአደባባይ ለማስተዋወቅ ሕጋዊ መብት ካለው አካል ፈቃድ ማግኘት እና ስምምነት መፈፀም ግዴታው ነው። በስምምነቱ ውስጥ ደግሞ ማስታወቂያው በአደባባይ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ የሚቀመጥ የጊዜ ገደብ ይኖራል የሚል እምነት አለኝ። እናም የማስታወቂያው የአደባባይ የጊዜ ቆይታ እንደተጠናቀቀ ማስታወቂያው እንዲነሳ ይህ ሕጋዊ ፈቃድ ያለው አካል ማስገደድ አለበት። አሁን እየተመለከትን ያለነው ግን በርካታ ማስታወቂያዎች አንድ ጊዜ ከተሰቀሉ በኋላ የሚነሱት ሌላ በቦታው የሚሰቀል ማስታወቂያ ሲገኝ ብቻ ነው። ይሄንን ለማረጋገጥ ለተወሰነ ጊዜ በከተማዋ ውስጥ ዞር ዞር ማለት በቂ ነው። ከተማዋን አጥለቅልቋት የሚታየው እንዲህ ዓይነት ማስታወቂያ ነው።

አቶ እንዳለ - ከሰሜን ሆቴል

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us