መወነጃጀሉ ህብረተሰቡን ይጎዳዋል

 

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እስካሁን ካከናወናቸው ተግባራት መካከል አንዱ ለከተማ አገልግሎት የሚውሉ ቢሾፍቱ አውቶቡሶችን ማቅረብ ነው። በዚህም መሠረት ለአዲስ አበባ አንበሳ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት አውቶብሶችን አስረክቧል። ይሁንና እነዚህ አውቶብሶች በየጊዜው እክል እየገጠማቸው ከአገልግሎት ውጪ ሲሆኑ እናያለን። ሰሞኑንም እንደተሰማው በአሁኑ ወቅት 195 አውቶብሶች አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ነው። ለዚሁ ደግሞ ድርጅቱ የአውቶብሶቹ የጥራት ችግር ነው ሲል ኮርፖሬሽኑ በበኩሉ የአያያዝ ችግር ነው እያለ አንዱ ሌላውን እየወነጀለ ቀጥለዋል። እንደሚገባኝ ከሆነ ሁለቱም አካላት ለህዝብ ምርትና አገልግሎታቸውን የማቅረብ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ስለሆነም ሁለቱም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው። አንዱ በሌላው በማመካኘቱ የሚጠፉ ስህተት አይኖርም። ስለዚህ እያንዳንዱ የየራሱን ጥፋት አምኖ ተቀብሎ የሚጠበቅበትን ስራ መስራት ይኖርበታል። ይሄ የሚሆነውም ሁለቱም አካላት ለህዝብ እንደቆመ ተቋም ተቀራርበው በመነጋገር ችግሩን መቅረፍ ሲችሉ  ነው። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር እነዚህ ተቋማት ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት በሚወነጃጀሉበት ወቅት በመካከል የሚጎዳው ህብረተሰቡ ነው። የከተማ ትራንስፖርት ችግር የእያንዳንዳችንን ቤት እያንኳኳ ባለበት በአሁኑ ወቅት ይህን ያህል ቁጥር ያለው አውቶቡስ ስራ ፈትቶ መቆም ማለት ምን ያህል አሳፋሪ እንደሆነ መገመት ቀላል ነው። ተጨማሪ መጓጓዣዎችን ማፈላለግ ሲያስፈልግ ያሉትን እንኳን በአግባቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ አለመቻል ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣትን ያሳያል።

 

አውቶቡሶቹ ሲሰሩ ከ15 እስከ 20 ዓመት አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ ታስቦ ነው ተብሏል። ታዲያ በምን ምክንያት ነው ለአምስት ዓመት እንኳን ሳያገለግሉ ከአገልግሎት ውጪ ሊሆኑ የቻሉት? የሚለው ነገር ጥልቅ ምርመራ ያስፈልገዋል። እነዚህ አውቶቡሶች የሚያጓጓዙት የሰው ልጆችን እንደመሆኑ መጠን አገልግሎት ካለመስጠታቸው ውጪም በስራ ላይ ያሉትም ከምርት የጥራት ጉድለት ጋር ተያይዞ አደጋ ስላለማድረሳቸው ማረጋገጫ ሊኖር ይገባል። ካልሆነ ግን ነገም የሰው ህይወት ከጠፋ በኋላ አንዱ በሌላው እያሳበበ የሰው ህይወት በከንቱ የማይቀርበት ምክንያት አይኖርም። ከዚህ በተጨማሪም የመለዋወጫ እቃ ግዢን በተመለከተ ውጭ ሀገር ድረስ የሚያስኬድ አሳማኝ ምክንያት መኖር አለመኖሩን ማጣራት ያስፈልጋል። ካልሆነ ግን ከዚህ ቀደም እንደተሰሙት አይነት የተዝረከረኩ እና ብልሹ አሰራሮች ላለመስፋፋታቸው ማረጋገጫ አይኖርም።

 

                  እውነቱ ያለው - ከመገናኛ አካባቢ የተሰጠ አስተያየት

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us