ሰፊ መረጃ ቢሰጠን?

በተደጋጋሚ በሀገራችን በተከሰተ ድርቅ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለረሃብ ተጋልጠው ነበር። በአሁኑ ወቅት በተወሰነ ደረጃ መሻሻል እያሳየ መሆኑን እየሰማን እንገኛለን። አንዳንድ ክልሎችም የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ሪፖርት እያደረጉ ይገኛሉ። ነገር ግን አሁን ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ በቂ መረጃ እያገኘን አይደለም። ከዚህ ቀደም በአንዳንድ ክልሎች ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል መንግስትም ከቁጥጥሩ ውጪ እንዳይወጣ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ሲናገር ተሰምቷል። ሆኖም ግን ድርቁ ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ ለህዝቡ የደረሰ ዝርዝር መረጃ የለም። በኛ ሀገር ብዙ ጊዜ የተለመደው ችግር ከተባባሰ በኋላ ችግሩን ለማስተባበል መሞከር ነው። በዚህ ጉዳይ ግን እንዲህ አይነት መሸፋፈን የሚያዋጣ አይደለም። የሚከፈልበት ዋጋ የሰው ህይወት ስለሆነ ቀደም ብሎ ለህዝቡ በቂ መረጃ መስጠት ያስፈልጋል። ተመሳሳይ ችግር ድጋሚ እንዳይፈጠርም ህብረተሰቡ ያገኘውን ምርት በአግባቡ መጠቀም የሚችልበትን ሁኔታ በተመለከተ የባለሞያ ድጋፍ ቢደረግለት አይከፋም። የአየር ንብረት ለውጡ በዚህ የማያቆም እና ሊቀጥል የሚችል እንደሆነ አንዳንድ አካላት እየተነበዩ ስለሆነ ቅድመ ጥንቃቄዎችን ማድረግ እና በዚህ ረገድ ሊያግዙ የሚችሉ አካላትንም ቀደም ብሎ በጋራ ለመስራት ማግባባት የችግሩን ግዝፈት ለመከላከል ያግዛል። ከዚህ በተረፈም ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢ ነዋሪዎች በአማራጭ የስራ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ፣ ችግር እንኳን ቢመጣ ህይወታቸውን መታደግ የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር ይቻላል። የመገናኛ ብዙሃንም ችግሩ ጫፍ ላይ ሲደርስ ከመረባረብ ይልቅ ለህዝቡ በቂ እና ትክክለኛ መረጃን በማድረስ ለወገን ያላቸውን አለኝታነት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us