መግዛት ወይስ መጠገኑ ያዋጣ ይሆን?

በሀገራችን በተለይ በአዲስ አበባ ያለውን የትራንስፖርት እጥረት ለመቅረፍ እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች መካከል አንዱ አውቶቡሶችን መግዛት ነው። መንግስትም በተደጋጋሚ እያደረገ ያለው ነገር ይሄንኑ ነው። በቅርቡ በርካታ ቁጥር ያላቸውን አውቶቡሶች ገዝቶ ወደ ዘርፉ እንደሚያስገባ መንግስት ባለፈው አስታውቋል። ኃላፊነቱን በመወጣቱ መንግስት ሊመሰገን ይገባዋል። ነገር ግን ይህ የአውቶቡስ ግዢ ብዙ ጊዜ ያስከተላቸው ጣጣዎች አሉ። ከዚህ በፊት እንዳየነው የሚገዙት አውቶቡሶች ጥራታቸው ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ ያገለግላሉ ከተባለው ጊዜ በግማሽ ባነሰ ጊዜ ውስጥ እየተበላሹ እና ከአገልግሎት ውጪ እየሆኑ ነው። በዚያ ላይ አንድ ጊዜ መለዋወጫ የለም ሌላ ጊዜ ደግሞ ኃላፊነቱ የኔ አይደለም በሚል ውዝግብ ብልሽታቸው ተጠግኖ ወደ አገልግሎት መግባት እንኳን ሳይችሉ የተቀመጡ በርካታ አውቶቡሶች አሉ። በነገራችን ላይ ከዚህ ቀደም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተበላሽተው የቆሙና ለመጠገን አንዱ ወደ ሌላው እያላከከ ተገትረው የቀሩት የቢሾፍቱ አውቶብሶች ጉዳይ ከምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የምናውቀው ነገር የለም። አውቶብሶቹ ተጠግነው ወደ ስራ ገብተው ይሁን ወይ ደግሞ እዚያው ቆመው ዝናብና ፀሀይ እየተፈራረቀባቸው ይሁን የሚያውቁት እነርሱ ብቻ ናቸው። የእነዚህኞቹ አውቶብሶች ጉዳይ መፍትሄ ሳያገኝ አሁን ደግሞ ሌሎች አውቶብሶች ሊገዙ መሆኑ ዜና ተነግሮናል። ያሉትን ጠግኖ ወደ አገልግሎት ማስገባቱ ነው ወይስ አዲስ መግዛቱ ነው አዋጪው? የሚለውን ጥያቄ ራሱ መንግስት ይመልሳል። ነገር ግን እነርሱ አድበስብሰው ቢያልፉትም እኛ እንደማንረሳው ሊያውቁት ይገባል። 

 

                           ቃል ኪዳን ተካልኝ - ከአዋሬ

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us