ዜጋን እየገደሉ መቀጠል

 

በአዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከሚማሩ የ2ኛ እና የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ከግማሽ በላዮቹ ፅሁፍ ማንበብ እንደማይችሉ የከተማዋ የትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ ባደረኩት ጥናት አረጋግጫለሁ ብሏል። ይሄ ምን ማለት እንደሆነ የሚገባው ከአፉ ላይ ነጥቆ ለልጁ የትምህርት ቤት እየከፈለ ለሚያስተምር ወላጅ ነው። በከተማ አካባቢ አሁን ባለው ሁኔታ አንድ ልጅ ሁለተኛ ክፍል ደረሰ ማለት የመዋዕለ ህፃናት ቆይታውን ጨምሮ  ቢያንስ አምስት አመታትን በትምህርት ገበታ ላይ አሳልፏል። ታዲያ በአምስት ዓመታት የትምህርት ቤት ቆይታው ማንበብ አለመቻል ማለት ምን ማለት ነው? እንኳን አዲስ ነገርን ለመያዝ ፈጣን አእምሮ ያላቸው ታዳጊዎች ቀርተው አዋቂ ሰውም ቢሆን በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ማንበብና መፃፍ የማይችልበት ምክንያት አይኖርም። አሁን እየተሰማ ያለው ነገር ግን አስደንጋጭም አሳዛኝም ነው። አንድ ልጅ ወደ ትመህርት ቤት ሲሄድ የመጀመሪያ አላማው ማንበብና መፅፍን መልመድ ነው። ሌሎች ሌሎች ነገሮች ከዚህ ቀጥለው የሚመጡ ናቸው። ታዲያ እነዚህ ልጆች ምን ሲሰሩ እየዋሉ ነው ማንበብ እንኳን ያቃታቸው? ለእነዚህ ተማሪዎች የተመደቡ መምህራንስ ምን ሲሰሩ ነው የሚውሉት? ተደጋግሞ እንደሚባለው ትምህርት ቤቶች ቀጣይ ሀገር ተረካቢ ዜጐች የሚፈጠሩባቸው የሁሉም መሠረት የሆኑ ተቋማት በመሆናቸው ከፍተኛ ጥንቃቄን ይጠይቃሉ። በተለይ ህፃናት እና ታዳጊዎች ደግሞ በለጋ እድሜያቸው እና በንፁህ አእምሯቸው ሊቀበሏቸው የሚችሏቸውንና የሚገባቸውን ነገር አግኝተው ማደግ ካልቻሉ በኋላ ላይ ለማስተካከል የሚደረገው ጥረት እጅግ አድካሚ ነው የሚሆነው። ምክንያቶቹ ምንም ይሁኑ ምንም እያንዳንዱ ትምህርት ቤት ተፈትሾ ህፃናት እድሜያቸውን የሚወጥን እውቀትና ግንዛቤ ኖሯቸው እንዲያድጉ የማድረጉ ጉዳይ ሊተኮርበት ይገባል። አንድ ልጅ ፊደልን ማንበብ ሳይችል እንዴት ሆኖ ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላኛው ሊያልፍ ይችላል? የሚለው ጉዳይ ከስር መሠረቱ መፈተሽ የሚያስፈልገው ይመስለኛል። ካልሆነ ግን ትምህርት ቤቶቹ ዜጐችን እየገደሉ መቀጠላቸው አይቀሬ ነው።

አቶ ስንታየሁ - ከቄራ¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us