You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት የአፍሪካ አገራትን ባለፈው ሳምንት የጎበኙትን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰንን ከሥልጣን ማንሳታቸው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ትላንት በትዊተር ገጻቸው አስታወቁ። በምትካቸውም የሲአይኤ ዳይሬክተር ማይክ ፖምፒዎ እንደተኩ ገልጸዋል።

 

በሲአይኤ ዳሬክተርነት ሥፍራም የመጀመሪያዋ ሴት የሆኑትን ጊና ሀስፖልን መሾማቸው ተሰምቷል።


የኤክሶን ሞቢል ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ቲለርሰን የተሾሙት ከአንድ ዓመት በፊት መሆኑ አይዘነጋም።

በኢትዮጵያ እስከ ታህሳስ 2011 ዓ.ም የምግብ እህል እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ37 በመቶ በመጨመር 7 ነጥብ 8 ሚሊየን መድረሱን መንግሥትና ለጋሾች በትላንትናው ዕለት አስታወቁ፡፡

 

በዚሁ መሰረት በቀጣይ አንድ ዓመት በድርቅ የተጎዳው ተረጂ ወገን ቁጥር 7 ሚሊየን 880 ሺ 446 መሆኑንና ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብም 1 ነጥብ 4 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግ ይፋ ተረጋግጦአል፡፡

• ገዳሙ እንዲታደስ የእስራኤል መንግሥት ቃል ቢገባም፣ ኮፕቶቹ ዕንቅፋት ኾነዋል
• “ልቀቁና በራሳችን እናድሰው” ያሉትን መንግሥትም ቤተ ክርስቲያንም ተቃውመዋል
• ፖፑ፥ “ጠቅላላ ገዳሙ የእኛ ነው፤ መመለስ አለባችሁ፤” ብለው ለኢትዮጵያ አቻቸው ጻፉ
• “ኢትዮጵያውያን የታሪክና የቅድስና አንጡራ ሀብታችን ነው፤ አያገባችሁም፤” /ፓትርያርኩ/
• በኢትዮጵያ ቅርስነቱ መንግሥት እንዲጠብቀው፣ ፓትርያርኩ ጠየቁ

በክርስትና አስተምህሮና ሥርዐት ባላቸው አንድነት፣ የ“ኦርየንታል ኦርቶዶክስ” ቤተሰብ የሚባሉት የኢትዮጵያ እና የግብጽ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት፣ በጥንታዊቷ ኢየሩሳሌም ከሚገኘው የዴር ሡልጣን ገዳም እድሳት ጋራ በተያያዘ እየተበላሸ መኾኑን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናገሩ፡፡


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የካቲት 24 ቀን ከተከበረው አምስተኛ ዓመት የፕትርክና በዓለ ሢመታቸው ጋራ በተያያዘ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቴሌቪዥን ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በከፋ እርጅና እየፈራረሰ የሚገኘው የዴር ሡልጣን ገዳምና የመነኰሳቱ ማረፊያ ቤት እንዳይታደስ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን እንቅፋት በመፍጠሯና ከዚያም አልፋ ጠቅላላ ይዞታውን ለመንጠቅ እየቃጣች በመኾኑ፣ የሁለቱ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት እየተበላሸ ነው፤ ብለዋል፡፡


የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅት ገዳሙን ለማደስ ቃል መግባታቸውንና ይህንንም በጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የእስራኤል ጉብኝት ወቅት ቢያረጋግጡላቸውም፤ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግን፣ “መንግሥት የሚላችሁን ትታችሁ እኛ እናድስላችሁ፤ በገንዘባችን፣ በመሐንዲሶቻችን በራሳችን እኛ እናድሰው፤” እያለች እንደኾነ ፓትርያርኩ ተናግረዋል፡፡


በጉዳዩ ላይ፣ “ዴር ሡልጣንን ለመጎብኘት ሔደን በኢትዮጵያውን መነኰሳት ተከልክለን ተባረርን፤” ካሉ ሁለት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ወደ መንበረ ፓትርያርኩ መጥተው ስሞታ እንዳቀረቡላቸው የጠቀሱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ “በእኛ ሥር ኹነው እንዲቀመጡ ንገሩልን፤ ንገሯቸውና መቆያ ቦታም እንሰጣችኋለን፤ ገዳሙን ልቀቁልንና እኛ እናድሰው፤” በማለት እንደጠየቋቸው አመልክተዋል፡፡


በፓትርያርኩ በኩል፣ “ያለፈው ይበቃችኋል” የተባሉት ሁለቱ ግብጻውያን ጳጳሳት፣ “ሳንመካከር፣ ሳንወያይበት እድሳት የሚባል ነገር እንዳይደረግ” በሚል ሊያስጠነቀቁ ቢሞክሩም ተቀባይነት ባለማግኘታቸው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ፖፕ አባ ታዎድሮስ ማሳወቃቸውንና ፖፑም፣ የጳጳሳቱን አቋም በማጠናከር እድሳቱን ከመከልከላቸውም በላይ “ጠቅላላው ገዳሙ የእኛ ነው፤ መመለስ አለባችሁ፤” የሚል ደብዳቤ እንደጻፉ አቡነ ማትያስ በቃለ ምልልሱ አውስተዋል፡፡


ዴር ሡልጣን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የታሪክና የቅድስና አንጡራ ሀብት እንደኾነ በመጥቀስ ለፖፑ ደብዳቤ ምላሽ የሰጠችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ እድሳት ከባለቤትነት ጋራ የሚያያዝ እስከኾነ ድረስ በቱሪስትነት እንጅ በባለቤትነት ታሪክ የማያውቃት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን በእድሳቱም ጉዳይ የሚያገባት ነገር እንደሌለ መግለጿን አቡነ ማትያስ አስታውቀዋል፤ “ምንም ጸጸትና ርኅራኄ የሌላቸው ናቸው፤” በማለት ግብጾቹን ክፉኛ የወቀሱት ፓትርያርኩ፣ መንግሥት በኢትዮጵያ ቅርስነቱ ጥበቃ እንዲያደርግ በቃለ ምልልሳቸው ጠይቀዋል፡፡


ፓትርያርኩ ከሁለት ዓመት በፊት እስራኤልን በጎበኙበት ወቅት፣ “ምንም ቢሆን መነጋገር የማይፈታው ነገር የለምና እንነጋገርበታለን፤ ጉዳዩን እንፈታዋለን፤” የሚል ተስፋ ከሀገሪቷ ፕሬዝዳንት የተሰጣቸው ሲሆን፤ አምባሳደሩ አቶ ህላዌ ዮሴፍ ደግሞ፣ በኤምባሲው ዓመታዊ ዕቅድ ውስጥ የዴር ሡልጣን ጉዳይ ከዋነኛ ተግባራት አንዱ ኾኖ ተቀምጦ፣ ዋና መሥሪያ ቤቱም ክትትል እንደሚያደርግበት መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡

መጋቢት 03 ቀን 2010 ዓ.ም፤ ከመካነ ሠላም ተነስቶ ወደ ደሴ ሲጓዝ የነበረ ኮድ 3 አማ 12405 የሆነ አገር አቋራጭ አውቶቡስ በለጋምቦ ወረዳ ከገነቴ ከተማ በቅርብ ርቀት አቧራ ጥግ የሚባለውን ጠመዝማዛ መንገድ እንደጨረሰ መንገዱን ስቶ በመውደቁ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ የከፋና አሰቃቂ አደጋ መድረሱ ተሰማ።

 

አውቶቡሱ ከመካነ ሰላም፣ ከወግዲ፣ ከሳይንትና ከለጋምቦ ወረዳዎች ከመጫን አቅሙ በላይ ተሳፋሪዎችን ጭኖ እንደነበርና የመኪናው መገልበጥ መንስኤ ይኽው ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።


አብዛኞቹ ተሳፋሪዎችም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ነበሩ ተብሏል። ከተሳፋሪዎች መካከል 28 ወንድና 10 ሴት በድምሩ 38 ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን ቀሪዎቹ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በአቀስታ ከተማ ህዳር 11 ሆስፒታል እና ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ወዲያውኑ መወሰዳቸው የለጋምቦ ወረዳ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዘገባ ያስረዳል።

 

የኢትዮጵያ መንግስት እንደዚሁም ዲፒ ወርልድ የበርበራ ወደብን ድርሻ በመውሰድ አልምተው ለመጠቀም በቅርቡ ከሶማሌላንድ ጋር የደረሱትን ስምምነት የሶማሊያ መንግስት የሚቃወም መሆኑን ገለፀ፡፡ 

 

እንደ አፍሪካን ኒውስ ዘገባ ከሆነ ሶማሊያ ተቀውሞዋን የገለፀችው ስምምነቱ የሶማሊያን ሉዑላዊነት የሚጥስ ነው በማለት ነው፡፡ እንደዘገባው ከሆነ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ 19 በመቶውን ድርሻ ስትወስድ ዲፒ ወርልድ በአንፃሩ 51 በመቶውን ይይዛል፡፡ ቀሪው 30 በመቶው በሶማሊላንድ እጅ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ይሄንኑ የሶማሊያ ፌደራል መንግስትን የተቃውሞ አቋም የሶማሌላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ውድቅ አድርገውታል፡፡ ሶማሌላንድ የሶማሊያን እርስ በእርስ ግጭት ተከትሎ የሰይድ ባሬ መንግስት ከተወገደ በኋላ የራሷን ነፃነት ያወጀች ሀገር ናት፡፡


ሶማሌላንድ ከዚህም በተጨማሪ ራሷን ያደራጀች፣ የመገበያያ ገንዘብን ያሳተመችና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ሀገራዊ እውቅና እንዲሰጣት በተደጋጋሚ ጥያቄ በማቅረብ ላይ ያለች ናት፡፡ ሆኖም የሶማሊያ ፌደራል መንግስት መቋቋሙን ተከትሎ ሶማሌላንድ የሶማሊያ አካል መሆኗን በተደጋጋሚ እየገለፀ ይገኛል፡፡


ዜናው ሰሞኑን በሰፊው መራገቡን ተከትሎም ‹‹ስምምነቱ የሶማሊያን ሉአላዊነት ይጥሳል›› በማለት የዓረብ ሊግ ግልፅ ተቃውሞውን ያሰማ መሆኑን ኦል አፍሪካን ዶት ኮም በዘገባው አስታውቋል፡፡ የሶማሊያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ አዋድ የአረብ ሊግን አቋም በደስታ ተቀብለውታል፡፡ በዚህ ዙሪያ በኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ በዲፒ ወርልድ በኩል የተሰጠ አስተያየት የለም፡፡

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቃቂ ቃሊቲ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት ባለቤቱን ኢ- ሰብዓዊ በሆነ መንገድ የገደለውን ተከሳሽ ታጠቅ ፍቃዱ ገ/ፃዲቅ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ቀጣ።

 

የክስ መዝገቡ እንደሚያስረዳዉ ተከሳሽ የኢ.ፊ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539/1/ሀ/ ላይ የተመለከተዉን በመተላለፍ መጋቢት 01 ቀን 2009 ዓ.ም በግምት ከጥዋቱ 1 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ሲሆን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ክልል ልዩ ቦታው ቀይ አፈር መሸጋገሪያ ድልድይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የግል ተበዳይ እልፍነሽ በቀለን ስድስት ሜትር ጥልቀት ባለው ገደል ውስጥ በመወርወር፣ ነውረኝነትንና ጨካኝነትን በሚያሳይ ሁኔታ ህይወቷ እንዲያልፍ ያደረገ በመሆኑ በፈፀመው ከባድ የግድያ ወንጀል ተከሷል።


የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ተከሳሽ በፈፀመዉ ወንጀል ተጠያቂ መሆን የሚችልበትን በፖሊስ የምርምራ መዝገብና የሰዉ ምስክሮች፣ አስከሬን ምርመራ ዉጤት መግለጫ ማስረጃ በማያያዝ ለፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቃቂ ቃሊቲ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት አቅርቧል::


ተከሳሽ በችሎት ቀርቦ ክሱ ተነቦለት እንዲረዳው ከተደረገ በኋላ የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ ድርጊቱን ፈፀሜያለሁ ጥፋተኛ ነኝ በስሜት ውስጥ ገብቼ ያደረኩት እንጂ ጨካኝ ሆኜ አይደለም በማለት ተናግሯል።


የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ተከሳሽ በተከሰሰበት የወንጀል ድርጊት ያመነ በመሆኑ ሌላ ማስረጃ መስማት ሳያስፈልግ የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዲሰጥ በማለት ለፍርድ ቤቱ አስተያየት ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን መርምሮ ተከሳሹ በተከሰሰበት ወንጀል መሠረት ጥፋተኛ ነህ ብሎታል::


የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቃቂ ቃሊቲ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት የካቲት 07 ቀን 2010 ዓ.ም በዋለዉ ችሎት መዝገቡን መርምሮ በተከሰሰበት ክሰ ሪከርድ ያልቀረበበትና እጁን ለፖሊስ የሰጠ በመሆኑ በማቅለያነት በመቀበል ድርጊቱን በትዳር አጋሩ ላይ በመፈፀሙ በማክበጃነት በመያዝ ተከሳሹን ያርማል፣ ሌሎችንም ያስተምራል በማለት በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል ሲል የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የላከልን ዘገባ ያስረዳል። 

 

በይርጋ አበበ

 

የፓርኪንሰን ታማሚዎች በኢትዮጵያ ያው መድሃት ስርጭት፣ ዋጋ ንረት እና ከገበያ አለመገኘት ስጋት እንደሆነባቸው ተናገሩ። 


ለህመምተኞቹ ችግር መባባስ ዋናው ምክንያት በኢትዮጵያ ፓርኪንሰንን የሚመለከት ጥናት አለመካሄዱ መሆኑን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል። የፓርኪንሰን በሽታ በባህሪው ታማሚዎቹን የአካል እንቅስቃሴ፣ የእጅ ተግባር እና ንግግር የሚያደናቅፍ በመሆኑ ተማሚዎቹ ለዘርፈ ብዙ ችግር ተጋላጭ ናቸው። 


በዚህ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን ሃሳባቸውን የሰጡት በኢትዮጵያ የፓርኪንሰን ፔሸንትስ ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን መስራች ወይዘሮ ክብራ ከበደ፤ “በሽታው እኛን ታማሚዎቹን ከአካል እንቅስቃሴ ሃሳብን እስከመግለጽ ድረስ የሚገታ በመሆኑ ችግራችንን የሚያውቅልን የለም” ሲሉ ተናግረዋል። ወይዘሮ ክብራ አያይዘውም፤ በሽታው መድሃኒት የሌለው መሆኑን ተከትሎ ለህሙማኑ ተስፋ የሚሆነው በወዳጅ ዘመድ እንክብካቤ ማግኘት ቢሆንም በተለይ በኑሮ ደረጃቸው ዝቅ ያሉ ሰዎች በሽታው ሁሉንም ነገራቸውን እንደሚጎድልባቸው ገልጸዋል።


ፓርኪንሰን ህመም መሆኑ ታውቆ ለታማሚዎቹ የተለያዩ መድሃኒቶች (በሽታውን ፈጽሞ ማዳን ባይችሉም) መመረት እና ክትትል መደረግ ከጀመረ ከ200 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። በዚህም በዓለም ላይ በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የበሽታው ተጠቂ መሆናቸው ሲታወቅ፤ በኢትዮጵያ ግን ምን ያህል ታማሚዎች እንዳሉ መረጃው የለም። እስካሁንም በፓርኪንሰን ዙሪያ መንግስት የሰራው ጥናት አለመኖሩን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ዳይሬክተሩ አቶ አበባው አያሌው ተናግረዋል። 


በሽታው በሁሉም የዕድሜ ክልል፣ በሁለቱም ጾታ፣ በሁሉም የአካባቢ እና የአየር ንብረት የሚኖሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ቢሆንም እስካሁን በሽታው እንዳለባቸው አውቀው ማህበር መስርተው ህክምና እየወሰዱ ያሉ ዜጎች ብዛት 500 ብቻ ናቸው። እነዚህ ህሙማን ደግሞ ሁሉም የሚገኙት አዲስ አበባ ከተማ ብቻ መሆኑን ወይዘሮ ክብራ ተናግረዋል። በፓርኪንሰን ዙሪያ በኢትዮጵያ ጥናት ቢካሄድ የህሙማኑ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆን ግምታቸውን ገልጸዋል። 


በኢትዮጵያ የፓርኪንሰን ፔሸንትስ ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን የ2010 አምባሳደር አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ በበኩሉ የበሽታውን አስከፊነት ገልጾ በተለይ በኢኮኖሚ ደረጃቸው አነስተኛ የሆኑ ታማሚዎች የሚኖሩት ኑሮ አስከፊ መሆኑን ተናግሯል። ለዚህ ደግሞ ሁሉንም የበሽታው ተጠቂዎች በአንድ ጣራ ስር የሚያሳርፍ መጠለያ ለመገንባት በማህበሩ በእቅድ ደረጃ መያዙን ገልጾ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለዚህ በጎ አላማ ከታማሚዎቹ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል። 


ፓርኪንሰን ካጠቃቸው ታዋቂ ሰዎች መካከል በኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት የኖሩትና የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ደራሽ የሚባሉት የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓክረስት አንዱ ሲሆኑ፤ ታዋቂው ቦክሰኛ መሀመድ ዓሊ ደግሞ ሌላው ተጠቃሽ ነው። 


በኢትዮጵያ የፓርኪንሰን ፔሸንትስ ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን ሚያዝያ 6 ቀን 2010 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ በአዲስ አበባ የእግር ጉዞ ያካሂዳል።

ዶክተር አብይ አህመድ ዓሊ ማን ናቸው?

 

ዶ/ር አብይ አህመድ በአሁኑ ወቅት የኦህዴድ ሊቀመንበር ናቸው። ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት በዕጩነት ከቀረቡ ተወዳዳሪዎች አንዱ መሆናቸውም ይታወቃል። በአንባቢዎቻችን ጥያቄ መሠረት ሙሉ ፕሮፋይላቸውን በዚህ መልኩ አሰናድተነዋል።


ሙሉ መረጃውን ፖለቲካ ዓምድ ላይ ይመልከቱ

እየተጋጋለ የመጣውን ሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ «የመፍትሔው አካል መሆን አለብኝ» በሚል ራሳቸውን ከገዥው ፓርቲ ሊቀመንበርነት እና ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ያሰናበቱት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተገቢው ጥቅማ ጥቅማቸው የሚከበርላቸው መሆኑን ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የሕግ ባለሙያዎች ጠቆሙ።

 

ከኃላፊነት የተነሱ የሀገርና የመንግሥት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የምክርቤት አባሎች እና ዳኞች የሚያገኙዋቸው መብቶችና ጥቅሞች በሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 653/2001 በኃላም በአዋጅ ቁጥር 934/2008 እንደተሻሻለው መሠረት አቶ ኃይለማርያም የመቋቋሚያ አበል ክፍያ፣ በኃላፊነት በነበሩ ጊዜ ይከፈላቸው የነበረ የወር ደመወዝና አበል ከኃላፊነታቸው ከተነሱ በኃላም ሳይቋረጥ የሚቀጥል ይሆናል።


በተጨማሪም በሥራ ላይ የሚገኘው ጠቅላይ ሚኒስትር የደመወዝና የአበል ማስተካከያ ሲደረግለት ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትርም በተመሳሳይ ሁኔታ ማሻሻያ እንደሚደረግላቸው አዋጁ ያዛል።

 

የመኖሪያ ቤት አገልግሎት በተመለከተ፣


ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው የሚያገለግል የሠራተኞች ወጪን ጨምሮ በመንግሥት ወጪ የሚተዳደር ከአራት እስከ አምስት ክፍሎች ያሉት የመኖሪያ ቤት እንደሚሰጣቸው በአዋጁ መደንገጉን ጠቁመዋል።

 

የሕክምና አገልግሎትን በተመለከተ፣


በመንግሥት ወጪ በአገር ውስጥ እና የውጭ አገር የተሟላ የሕክምና አገልግሎት በፈለጉ ጊዜ ያገኛሉ።

 

የግል ደህንነት ጥበቃ አገልግሎትን በተመለከተ፣


ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ደህንነት ሲባል ጠባቂዎች በመንግሥት ወጪ ይመደቡላቸዋል።

 

የፕሮቶኮል አገልግሎት፣


የዲፕሎማቲክ ፓስፖርትና የቪአይፒ አገልግሎት ያገኛሉ። ቀድሞ በስራ ላይ በነበሩ ጊዜ ያገኙ የነበረውን የሚመጥን በአገር ውስጥና በውጭ አገር ሙሉ የፕሮቶኮል አገልግሎት ያገኛሉ።

 

የተሽከርካሪ አገልግሎት


ደረጃቸውን የጠበቁ ሶስት የመንግሥት ተሸከርካሪዎች ይመደብላቸዋል። የተሽከርካሪው ሹፌር ደመወዝ፣ የነዳጅና የጥገና እንደዚሁም ሌላ ወጪ በመንግሥት ይሸፈናል። ለባለመብቱና ለቤተሰቡ ጥበቃ አገልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ዓይነትና ብዛት ጥበቃውን በሚያካሂደው አካል ይወሰናሉ።


የስልክ አገልግሎት፣


ወጪው በመንግሥት የሚሸፈን ሁለት መደበኛ ስልኮች በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ እና አንድ ለግሉ ይኖረዋል። ለጥበቃ የሚውሉ ስልኮች ዓይነትና ብዛት ጥበቃውን በሚካሂደው አካል የሚወሰን ይሆናል።

 

የቢሮ አገልግሎት፣


ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በተለያዩ ሕዝባዊ አገልግሎቶች ላይ ከተሰማሩ መኖሪያ ቤቱ በሚገኝበት ከተማ የቢሮ አገልግሎት ይሰጣቸዋል። ባለመብቱ የሚመርጣቸውና መንግስት ደመወዛቸውን የሚከፍላቸው አንድ ጸሐፊና አንድ ባለሙያ ይኖረዋል። ለቢሮው የሚያስፈልገው ኮምፒውተሮች፣ ሰልክ፣ ኢንተርኔት፣ ፖስታ እና የመሳሰሉት በመንግስት ተሟልተው ወጪያቸውም ይሸፈናል።


ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ድረስ በጥያቄያቸው መሠረት አሰናብቶ በምትካቸው በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የሚቀርብለትን አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር በመቀበል ቃለመሀላ ያስፈጽማል ተብሎ ይጠበቃል።


 

በኢህአዴግ ህገ ደንብ መሰረት 180 አባላት ያሉት ከእያንዳንዱ እህት ድርጅት 45 የሚወከሉበት ምክር ቤት አለው፡፡ የኢህአዴግ ምክርቤት የድርጅቱን ሊቀመንበር በሚስጥር ድምፅ ይመርጣል። በድምፅ አሰጣጡ ላይ 180 የምክር ቤት አባላት እኩል ድምፅ አላቸው።


በህገ ደንቡ መሰረት አራቱም ድርጅቶች የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር እጩ የማቅረብ መብት አላቸው። ለሊቀመንበርነት የሚወዳደሩት የድርጅቶቹ ሊቀመናብርት ይሆናሉ። በህገ ደንቡ መሰረት ሊቀመንበሩ የድርጅቱ የበላይ አስፈፃሚ መሆኑን ቢገልፅም በመንግስት ስልጣን ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል የሚል በግልፅ የተቀመጠ ደንብ የለም።


በተለምዶ አሰራራቸው የግንባሩ ሊቀመንበር በቀጥታ የኢትዮጵያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል፡፡ በተለይ ከሃምሳ በመቶ በላይ ድምጽ በፓርላማው ድርጅቱ ስላለው በቀላሉ መንግስት የመመስረት እድሉ ሰፊ ነው፡፡ በሌሎች ሀገራት ግን በጣም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በፓርላማ ከፍተኛ መቀመጫ ስለሚያገኙ ውድድሩ ቀላል አይደለም፡፡


የሰበሰብናቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሕወሓት ለሊቀመንበርነት ቦታ እጩ አያቀርብም፡፡ የሕወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የትግራይ ክልል በርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር መሾማቸውን ልብ ይሏል፡፡


ብአዴን በሊቀመንበርነት አቶ ደመቀ መኮንን እጩ አድርጎ ያቀርባል፡፡ ሆኖም ድርጅቱ፤ ባደረገው ግምገማ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ በመንግስትና በድርጅት የስትራቴጂክ ሊደርሺፕ አቅም ማነስ መስተዋሉን ይፋ አድርጓል፡፡ አቶ ደመቀ መኮንን የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆናቸው ለውድድር ቢቀርቡም፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ላይ የተሰጠው ግምገማ በእሳቸውም ላይ ተግባራዊ ስለሚሆን የመመረጥ እድላቸው አናሳ ነው፡፡


ኦህዴድ ለድርጅት ሊቀመንበርነት በእጩነት ዶክተር አብይ አህመድን ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኦሕዴድ የሚያቀርባቸው እጩ በትምህርት ዝግጅት እና በሥራ ልምድ ያላቸው ብቃት ተቀባይነቱ ከፍ ያለ ነው፡፡ የተማሩት የትምህርት ዘርፎችም በርከት ስለሚሉ ግንዛቤያቸው ከፍተኛ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ሰዓት በክልሎች መካከል በተደጋጋሚ እየተፈጠረ ባለው የድንበር ግጭት ብዙ ሕይወትና ቁሶችን ሀገሪቷ እያጣች በመሆኑ ከፍተኛ የግጭት አፈታት ትምህርትና ልምድ ያለው አመራር አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኦሕዴድ ያቀርባቸው እጩ የመመረጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የሶህዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ በመካከላቸው የተፈጠረው የድንበር ግጭት በጋራ ለመፍታት መስማማታቸው አፈፃጸሙን ለማፋጣን ያለው እድል ከፍተኛ ነው፡፡


ደኢሕዴድ አቶ ሽፈራው ሽጉጤን እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡ አቶ ሽፈራው በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ያሉበትንን ክልል ለረጅም ዓመታት ጊዜ መርተዋል፡፡ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ላይ ተሹመው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም በቅርብ ከትምህርት ሚኒስትርነት ቦታቸው እንዲለቁ የተደረገበት ፍጥነት ከአፈፃጸማቸው ጋር የሚገናኝ ከሆነ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ለመቀጠል ያዳግታቸዋል ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡


በአጠቃላይ ግን በሚስጥር የሚሰጠውን የድምጽ ውጤት ፓርቲዎቹ የሚሰጡት ትርጉም፣ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ካልያዙትና ካልመነዘሩት ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ከባድ ነው፡፡ በመመካከርና በመግባባት የሚፈጽሙት ከሆነ ግን፣ ለሰላምና ለመረጋጋት ያለው ፋይዳ ምትክ አልባ ነው፡፡

Page 1 of 103

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us