You are here:መነሻ ገፅ»ወቅታዊ
ወቅታዊ

ወቅታዊ (205)

- በታክሲ አገልግሎት የሚሰማሩ 10ኛ ክፍል ማጠናቀቅና ልዩ ሥልጠናን መውሰድ ይጠብቃቸዋል፣

- መንጃ ፈቃዱን ለአንድ ዓመት ያላሳደሰ እንደገና ፈተና ይቀመጣል፣

 

የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በትላንትናው ዕለት ከተመለከታቸው አጀንዳዎች መካከል የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድን የሚመለከተው አዋጅ ይገኝበታል። ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር እይታ የተመራለት ቋሚ ኮምቴ የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል፡፡ ም/ቤቱ ትናንት አዋጁን ተወያይቶ ለማፅደቅ አጀንዳ ይዞ የነበረ ቢሆንም፤ በድምፅ ማጉያ (ማይክራፎን) የቴክኒክ ብልሽት ምክንያት ስብሰባው ባለመካሄዱ አዋጁ ሳይፀድቅ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።


ረቂቅ አዋጁ በአንድ በኩል በሃገራችን በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የተሽከርካሪ ቁጥርና የማሽከርከር ፍላጎትን ታሳቢ ያደረገ በሌላ በኩል ደግሞ ብቃት በሌላቸው አሽከርካሪዎች ምክንያት በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚረዳና የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ የአሰጣጥ ሥርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥነት ባለው መልኩ ለመተግበር የሚያስችል መሆኑ ተጠቅሷል።


በተጨማሪም አሁን በሥራ ላይ ያለውን የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ አዋጅ ቁጥር 600/2000 ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን አስመልክቶ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ባለድርሻ አካላት የማሽከርከር ፍቃድ አሰጣጥ ሥርዓታችን ዳግም እንዲፈተሽ በተደጋጋሚ ይነሱ የነበሩና በጥናት የተለዩ ችግሮችን የሚያቃልል መሆኑ ታምኖበታል።


ረቂቅ አዋጁ የአሽከርካሪ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ለማግኘት የሚጠይቀው የዕድሜ እና የትምህርት ደረጃ መስፈርቶችን የማሽከርከር ሙያ ከሚጠይቀው ክህሎትና የኃላፊነት ደረጃ ጋር የተጣጣመ እንዲሆንም ይረዳል ተብሎ ይገመታል።


አዋጁ ደረጃውን የጠበቀና የማሽከርከር ልምድን ማዕከል በማድረግ ደረጃ በደረጃ ወደ ከፍተኛው የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ የአሰጣጥ ሥርዓት በመተግበር በአሁኑ ወቅት የሃገራችን በአሽከርካሪዎች የማሽከርከር ብቃት ማነስ እና የሥነ-ምግባር ጉድለት ምክንያት እየደረሰ ያለውን የህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ የሚያስችል ነው ተብሏል።


ረቂቅ አዋጅ ማንኛውም ሰው የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱን ከአነስተኛ ደረጃ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ወይም ከአንድ ምድብ ወደ ሌላ ምድብ ሲቀይር አዲስ በሚሰጠው የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ላይ ቀድሞ ይዞት የበረው የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ምድብ እና ደረጃ በሙሉ ሊያሽከረክር እንደሚችል ተገልጾ በቋሚ ኮምቴው ተሻሽሎ እንደሚሰጠው ተደንግጎአል።


በረቂቅ አዋጁ በታክሲ አገልግሎት ሥራ መሠማራት የሚፈልጉ አሽከርካሪዎች ልዩ ሥልጠና መውሰድ እንዳለባቸው ተደንግጓል። በዚህ አዋጅ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /1/እና /2/ የተገለፀው ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም አሽከርካሪ በታክሲ አገልግሎት የተመዘገቡ ተሽከርካሪዎችን ማሽከርከር የሚችለው፡-


ሀ/ 10ኛ ክፍልን ያጠናቀቀ ሆኖ የአውቶሞቢል ወይም የሕዝብ ምድብ ቋሚ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ያለው ከሆነ፤ እና


ለ/ ባለሥልጣኑ ባዘጋጀው የሥልጠና ይዘት መሰረት ከፈቃድ ሰጪ አካል ልዩ ሥልጠና በመውሰድ የታክሲ የአሽከርካሪ የምስክር ወረቀት የተሰጠው እንደሆነ ነው በሚል ተስተካክሎ እንዲጸድቅ ተደርጓል።


በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 4 እና 5 ላይ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ለማግኘት የሚያመለክት ማንኛውም ሰው ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ ደረጃ ለማሳደግ ቢያንስ የአንድ ዓመት የማሽከርከር ልምድ ሊኖረው እንደሚገባ አስገዳጅ ሆኖ ተደንግጓል። ነገር ግን የማሽከርከር ልምዱ የሚቆጠረው አሽከርካሪው ጊዜያዊ ወይም ቋሚ የአሽከርካሪነት ማረጋገጫ ፈቃድ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ እንደሆነ ረቂቅ አዋጁ በግልፅ አያስቀምጥም። ስለሆነም በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 4 እና 5 የተገለጸው የአንድ ዓመት ጊዜ የሚቆጠረው ቋሚ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ከያዘበት ቀን ጀምሮ እንደሆነ በግልጽ መደንገግ አስፈላጊ በመሆኑ በሚከተለው መልኩ ተስተካክሏል።


በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 15 ላይ ፈቃድ ሰጪው አካል የቀረበለትን ማመልከቻ መርምሮ በአዋጁ አንቀጽ 8፣ 12 እና 13 ድንጋጌዎች የተቀመጡ መስፈርቶችን መሟላታቸውን ካረጋገጠ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ የሚወስድ ከሆነ ከሕክምና ተቋማት ወይንም በሕግ ሥልጣን በተሰጠው አካል ተረጋግጦ የቀረበ ግዴታ ወይም ገደብ ካለ በፈቃዱ ላይ አስፍሮ የተጠየቀውን ምድብ ጊዜያዊ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ይሰጣል።


በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ የአገልግሎት ጊዜው ካበቃ በኋላ ባለው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሳያሳድስ የቀረ አሽከርካሪ የተግባር ፈተና ተፈትኖ ሲያልፍ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ እንደሚታደስለት የተቀመጠው በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ለተሰጠ ቋሚ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ብቻ እንደሆነ ያልተመላከተ በመሆኑ እና በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት የተሰጠ ጊዜያዊ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ የአገልግሎት ጊዜው ካበቃ በኋላ ባለው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሳያሳድስ የቀረ አሽከርካሪ በምን ሁኔታ ይስተናገዳል የሚለውን በግልጽ ያላመላከተ በመሆኑ ቋሚ እና ጊዜያዊ ፈቃዶችን ለያይቶ ማስቀመጥ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሚከተው ተሻሽሏል።


በአንቀጽ 19 (5) ላይ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) እና በዚህ አዋጅ አንቀጽ 15 (2) መሠረት የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ የአገልግሎት ጊዜው ካበቃ በኋላ ባለው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሳይቀይር ወይም ሳያሳድስ የቀረ አሽከርካሪ ፈቃዱ ቋሚ ከሆነ የተግባር ፈተና ተፈትኖ ሲያልፍ ይታደስለታል። ፈቃዱ ጊዜያዊ ከሆነ ደግሞ ከተግባር ፈተና በተጨማሪ ጊዜያዊ ፈቃዱን በያዘበት ዓመት የተመዘገበበት የጥፋት ሪከርድ ታይቶ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ይታደስለታል በሚል ተስተካክሏል። 

የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ያቋቋመው የሱፐርቪዥን ቡድን በግጭት ሲናጡ የከረሙትን የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎችን ሁኔታ በአካል ተመልክቶ ታህሳስ 26 ቀን 2010 ዓ.ም ሪፖርቱን ለምክርቤቱ አቅርቧል። “የሕዝቤ ጥቅም ተነክቷል” በሚል ኢህአዴግን ተቀይመው መልቀቂያ አስገብተው የነበሩት አቶ አባዱላ ገመዳ በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ውሳኔ ወደቀድሞ ሥራቸው ከተመለሱ በኋላ ይህንኑ መድረክ መርተዋል። የሱፐርቪዥኑ ቡድኑ ተልዕኮ ያተኮረው በኦሮሚያ እና በሶማሌ አጎራባች አካባቢዎች ባለፉት ጊዜያት በተፈጠሩት ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን በመስክ ሄዶ በመመልከት በተለይ ከሰብዓዊ ቀውስ አኳያ የደረሰውን ችግር ለምክርቤቱ ሪፖርት ለማድረግ ነው። ቡድኑ ይህን ትልቅ ተልዕኮ ይዞ 13 አባላትን በማቀፍ በ3 አቅጣጫ ወደሁለቱም ክልሎች ከጥቅምት 25 እስከ ህዳር 2 ቀን 2010 መንቀሳቀሱን ገልጿል።

 

የሪፖርቱ አንኳር ነጥቦች


ግጭቱ ከታህሳስ 2009 ዓ.ም ጀምሮ መከሰቱን፤ ነገር ግን ይህ ቡድኑ የመስክ ምልከታ ባደረገባቸው ግዜያት በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ተፈናቃዮች በቂ ዕርዳታና ድጋፍ ሳያገኙ በከባድ ቀውስ ሆነው መመልከቱን፣ በዚህም ምክንያት ዜጎች በመንግሥት ላይ ያላቸው እምነት መሸርሸሩን ታዝቧል፡፡ በተጨማሪም ከሁለቱም ወገኖች በኩል ሞት፣ ከቤት ንብረት መፈናቀል፣ የአካል መጉደል፣ ጾታዊ ጥቃት... መድረሱን አመልክቷል።


ተፈናቃዮች ለዓመታት ለፍተው ያፈሩትን ሐብት፣ ንብረት፣ ገንዘባቸውን ጥለው ከመሰደዳቸውም በላይ የአንድ ቤተሰብ አባላት የተጠፋፉበት ሁኔታ ተከስቷል። ከእነዚህ ተፈናቃዮች መካከል የመንግሥት ሠራተኞች የነበሩ ግለሰቦች ያለደመወዝ ከእነቤተሰባቸው እየማቀቁ የሚገኙበት መሆኑን አጥኚው ቡድን አረጋግጧል።


የቡድኑ አባላት በስራ ላይ በነበረበት ወቅትም በግጭቱ የሰዎች ሞት፣ የእንስሳት መዘራረፍ፣ መፈናቀል ቀጥሎ ነበር። በዚህም ምክንያት ወገኖች በተፈናቀሉበትም ቦታ አለመረጋጋት መኖሩን፣ እናቶች በጫካ ውስጥ ጭምር ለመውለድ መገደዳቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል።


በተጨማሪም የምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕርዳታዎች በበቂ ሁኔታ አለመቅረብ፣ ለተፈናቃይ ወገኖች መቅረብ የነበረባቸው የትምህርት የጤና አግልግሎቶች በበቂ ሁኔታ እየቀረቡ አይደሉም ብሏል።


በአጠቃላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በከፍተኛ ደረጃ መታየቱን በመጠቆም የሰብዓዊ መብት ኮምሽን ጉዳዩን አጣርቶ እንዲያቀርብ ቡድኑ በውሳኔ ሀሳቡ ላይ አስፍሯል።


የቡድኑ ሪፖርት ህዳር 2 ቀን በየደረጃው ለሚመለከታቸው አካላት በቃልና በጹሁፍ መቅረቡን፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች ለምክርቤቱ ለማቅረብ አለመቻሉን ተጠቅሷል። ይህም ሆኖ የምክርቤቱ አባላት በሪፖርቱ ሳይቀርብ መዘግየት ደስተኛ አለመሆናቸውን ደጋግመው በሰጡት ሀሳብ አንጸባርቀዋል። አንዳንዶችም' ሪፖርቱ ግዜውን የጠበቀ አይደለም። ከዚህ የበለጠ ምን አጀንዳ ሊኖር ይችላል?' ሲሉ መረር ባለ ቃል ጠይቀዋል።


የቅኝት ቡድኑ ግጭቱ የሕዝብ ለሕዝብ አለመሆኑን አረጋግጫለሁ ማለቱን ተከትሎ የምክርቤቱ አብዛኛው አባላት እነዚህ ወንጀለኞች እነማንናቸው፣ ለምንድነው ለፍርድ የማይቀርቡት? የፌደራል መንግሥትስ ለምን ዝምታን መረጠ? በማለት አጥብቀው ጠይቀዋል። ‘መሸፋፈን ይቅር' ያሉ አባላት በወንጀሉ እጃቸው ያለበት ከፍተኛ አመራሮች ጭምር ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ሲሉ ጠንካራ አቋማቸውን ገልጸዋል።


በመድረኩ ላይ በግጭቱ ጉዳይ የተቋቋመው ብሄራዊ ኮምቴ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ የፌደራል አርብቶ አደር ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ፣ የመከላለያ ሚኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ የፌደራል ፓሊስ ኮምሽነር አቶ አሰፋ አብዩ፣ የብሄራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮምሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በትላንቱ የፓርላማ መድረክ በአስረጅነት ተገኝተዋል።


የፌዴራል አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ ግጭቱ መከሰቱ ከተሰማ በኋላ በፌዴራል መንግሥት በኩል ተከታታይ ውይይቶች መደረጋቸውን ያስታውሳሉ፡፡ የመጀመሪያው ጳጉሜ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የሁለቱ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች በተገኙበት በተደረገ ውይይት ክልሎቹ ግጭቱን እንዲያረጋጉ፣ የተዘጉ መንገዶች እንዲከፈቱ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ ሆኖም ግጭቱ ሊበርድ አልቻለም ብለዋል፡፡ አያይዘውም መስከረም 6 ቀን 2010 ዓ.ም የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጎሣ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ምክክር ተደረገ፡፡ የታሰበውን ያህል ግን ለውጥ አልመጣም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ከመስከረም 8 ቀን ጀምሮ የዕለት እርዳታ ሥራዎች መጀመራቸውን፣ ነገር ግን በየዕለቱ የተፈናቃዩ ቁጥር ይጨምር ስለነበር አቅርቦቱ በቂ አልነበረም፡፡ በግጭቱ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተም ሲያብራሩ እጅግ ከባድ፣ ዘግናኝ እና መቼም መደገም የሌለበት ነው ሲሉ ገልፀውታል፡፡


ዕርዳታ በወቅቱ ለምን ማድረስ እንዳልተቻለ አቶ ምትኩ ካሣ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮምሽነር በሰጡት ማብራሪያ መጀመሪያ ላይ የመረጃ ችግር ነበር። ምን ያህል ሰው ተፈናቀለ፣ የት ነው ያለውና የመሳሰሉ መረጃዎች ሳይሟሉ ዕርዳታ ማቅረብ አስቸጋሪ ነበር ብለዋል። ስራው በጸጥታ ችግርና በመንገዶች መዘጋት ምክንያት ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከአንድ ሳምንት በላይ ጭምር አንድ ቦታ ለመቆም የሚገደዱበት ሁኔታ አጋጥሟል። በተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃቶች መድረሳቸው የተሽከርካሪ ባለቤቶች አንሄድም እስከማለት አድርሷቸዋል፡፡


መልሶ ለማስፈር የሠላም ኮንፈረንስ መካሄድ ነበረበት፣ ይህን ማካሄድ ባለመቻሉ አልተሳካም ብለዋል።


የፌደራል ፓሊስ ኮምሽነሩ አቶ አሰፋ አብዩ የተጠያቂነት ጉዳይ ከሰብዓዊ መብት እና ከወንጀል አንጻር በሁለት መንገድ እየተሰራበት መሆኑን ጠቅሰዋል። ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ግብረ ሀይል አቋቁሞ ወንጀለኞችን ማደን ጀምሯል። በእስካሁኑ ሥራ ከወንጀሉ ጀርባ እንዳሉ የተጠረጠሩ የፖሊስ፣ የልዩ ሀይል፣ የሚሊሽያ፣ የወረዳ አስተዳደር አካላት መኖራቸውን ፍንጭ ሰጥተዋል። እስካሁን በኦሮሚያ በኩል 98 ተጠርጣሪዎች የተያዙ ሲሆን በሶማሌ ክልል በኩል የተያዙት 9 ብቻ መሆናቸውን ኮምሽነሩ ሲናገሩ የፓርላማ አባላት በስላቅ ሳቅ አጅበዋቸዋል። በአጠቃላይ ከሁለቱም ክልሎች ሌሎች 98 ያህል ተጠርጣሪዎች እንደሚፈለጉና የወንጀል ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ በመስጠት ረገድ ከባድ ችግር ማጋጠሙን ይፋ አድርገዋል።


ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች ቁጥር ወደ 126 ከፍ አድርገው ተናግረዋል። ክልሎቹ ተፈላጊ ወንጀለኞች ለፌደራል መርማሪ አካላት አሳልፎ የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው ማስጠንቀቂያ አዘል ንግግር አሰምተዋል። መንግሥት ኃላፊነቱን አልተወጣም ለሚለው ትችት በችግሩ ስፋት የሚመጥን እርምጃ አለመወሰዱን አቶ ደመቀም አምነዋል። ሆኖም ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ያሉበት ኮምቴ በማቋቋም ብዙ ስራዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል። ተሰርቷል ካሉት መካከል በግጭት አካባቢዎች ከማንኛውም የክልል ታጣቂ ሀይል ነጻ ማድረግ ተችሏል፣ በዚህም እርምጃ አንጻራዊ ሠላም እየመጣ ነው ብለዋል። የሠላም ኮንፈረንሱ ባለመሳካቱ ክልሎች በተመረጡ አካባቢዎች በግዜያዊነት ተፈናቃዮችን እንዲያሰፍሩ ወስነው እየተሰራበት ነው ብለዋል።


ፓርላማው የሱፐርቭዥን ቡድኑን ሪፖርት ጥቂት ማሻሻያዎች አክሎበት በ3 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ተቀብሎታል። 

የአጠቃላይ የብቃት ምዘና ፈተና አካሄድን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ሃሳቦችን ማንሸራሸር እጅግ ይጠቅማል 

ዶ/ር አረጋ ይርዳው

 

የትምህርት ሚኒስቴር በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም የመጨረሻ ሳምንት በተለይ ለሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች ባስተላለፈው ሰርኩላር ደብዳቤ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የቅድመ ምረቃ የትምህርት መርሃግብር ማጠናቀቂያ ላይ የአጠቃላይ የብቃት መለኪያ ወይንም የመውጫ ፈተና እንዲሰጥ አዟል። ቀደምሲል ይህ መርሃ ግብር በህግ እና በሕክምና ተማሪዎች ላይ ተግባራዊ መደረጉም የሚታወስ ነው። ይህንኑ መመሪያ መነሻ በማድረግ ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር እና የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት አነጋግረናቸዋል። ዶ/ር አረጋ ቀደም ሲል ለስምንት ዓመታት ያህል የግል የከፍተኛ ትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ማኅበርን በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ እንደመሆናቸው መጠን መመሪያው ከግሉ ዘርፍ አንፃርም እንዴት እንደሚታይ ሃሳባቸውን ገልፀዋል። መልካም ንባብ!

 

ሰንደቅ፡- የትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና አስመልክቶ ያወጣውን መመሪያ በአጠቃላይ እንዴት አገኙት?


ዶ/ር አረጋ፡- መመሪያውን አንድ ቦታ ላይ አግኝቼ እንደተመለከትኩት ጥቅምት 21 ቀን 2010 ዓ.ም ከትምህርት ሚኒስቴር የወጣ ነው። ደብዳቤው በቀጥታ የተፃፈው ደግሞ ለመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች ብቻ ነው። የግል ዩኒቨርሲቲዎችንና ኮሌጆችን አላካተተም። ይህ ለምን እንደሆነ በግሌ አላወኩም። ምናልባት ተመሳሳይ ደብዳቤ ለግል ትምህርት ተቋማትም ተፅፎ ነገር ግን ሳልመለከተው ቀርቼ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የሚመለከት መመሪያ ግን ወጥ በሆነ መልኩ በመንግሥትም በግልም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተግባራዊ ቢሆን ጠቀሜታው የበለጠ ከፍ ያለነው። የትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በቅድመ ምረቃ ትምህርት መርሃ ግብር ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና እንደሚወስዱ ይገልፃል። ይህን ፈተና አንዳንዶቹ የመውጫ ፈተና ይሉታል፣ ሌሎቹ አጠቃላይ ምዘና ወይም የብቃት መለኪያ በማለት ይጠሩታል። አጠራሩ በራሱ ትንሽ ደብለቅለቅ ያለ ይመስላል። በትርጉም ደረጃ ግን አንዱ ከአንዱ ልዩነት አለው። ለአሁኑ ቃለመጠይቅ አጠቃላይ የምዘና ፈተና የሚለውን ወስደን መነጋገር እንችላለን። በመመሪያው መሠረት ፈተናው ተግባራዊ የሚሆነው ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ነው። እንግዲህ መመሪያው በ2011 ዓ.ም የሚተገበር ከሆነ ወደኃላ ተመልሶ በ2009 ዓ.ም ትምህርት የጀመሩ ተማሪዎችን የሚመለከት ይሆናል ማለት ነው። ይህ ስሌት እንግዲህ አንድ ተማሪ ዲግሪውን ለመውሰድ ሶስት ዓመት ሊፈጅበት ይችላል በሚል ያስቀመጥኩት መሆኑ ይታወቅ። መመሪያው ወደኋላ ሄዶ፣ ስለፈተናው ምንም መረጃ ያልነበራቸው ተማሪዎች ፈተና እንዲቀመጡ ያስገድዳል ማለት ነው። ይሄ በራሱ ችግር አለው ብዬ አስባለሁ። ፈተናው የግድ አስፈላጊ ከሆነ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከሚገቡ አዲስ ተማሪዎች ጀምሮ ሥራ መሠራት አለበት። በሂደት ላይ ያሉትን ተማሪዎች መካከል ላይ ተገብቶ እንዲህ ዓይነት ፈተና ውሰዱ ማለት ችግር ሊኖረው ይችላል። አንዳንድ ሰዎች ለፈተና ዝግጅት አያስፈልግም፣ ያለውን ነገር ነው የምንፈትነው ሊሉ ይችላሉ። በእኔ ዕይታ ፈተና አለ ብሎ መዘጋጀትና በድንገት መፈተን አንድ ናቸው ብዬ አላስብም።
ሌላው ዓቢይ ጉዳይ ግልፅነት ያስፈልገዋል ብዬ የማስበው ይሄ አጠቃላይ ፈተና ዲግሪን ለማግኘት እንደአንድ መመዘኛ (Requirement) ከሆነ ካሪኩለም ውስጥ መካተት አለበት። ክሬዲት ሰዓትም (hours) መታወቅ አለበት። ይሄ ከአሁን በፊት በሙከራ ላይ በነበሩት እንደ ሕግ እና ህክምና የትምህርት ዓይነቶች ላይ ተግባራዊ የሆነ ነው። አንድ ተማሪ ዲግሪ ለማግኘት የሚያስፈልገው አጠቃላይ ክሬዲት ሰዓት ይታወቃል። የመውጫ ፈተናውም ክሬዲት ሰዓት ተሰጥቶት ተምሮ ለፈተና መቅረብ አለበት። ካሪኩለሙም የአጠቃላይ የምዘና ፈተናውን ያካትታል ተብሎ መቀመጥ አለበት። አጠቃላይ የምዘና ፈተናው በካሪኩለም ከተቀረፀ መምህራን ያውቁታል፣ የዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች የአስተዳደር ሠራተኞች ያውቁታል፣ ለፈተናውም በቂ ዝግጅት ለማድረግ ይረዳል። መጨረሻ ላይ ውጤቱም ያማረ ሊሆን ይችላል።

 

ሰንደቅ፡- የአጠቃላይ ምዘና ፈተና በአንድ የሙያ ዘርፍ ተጨማሪ ብቃትን ከሚያስገኙ ፈተናዎች ይለያል?


ዶ/ር አረጋ፡- ፕሮፌሽናል ኤግዛሚኔሽን የሚባሉ አሉ። ለምሳሌ መሐንዲሶች የብቃት ፈተና ወስደው ፕሮፌሽናል መሐንዲሶች ይሆናሉ። አካውንታንቶች ፈተና ወስደው የተመሰከረላቸው የሂሳብ አዋቂ የሚል ሠርተፊኬት ያገኛሉ። የጤና ባሙያዎችም እንዲሁ ሠርቲፋይድ የሆኑ ባለሙያዎች ይሆናሉ። ሌላው እንዲሁ። ይሄ ሁሉም ባለሙያ ከዩኒቨርስቲ ተመርቆ ከወጣ በኋላ በራሱ ጥረት የሚያገኘውና አንዱ ከሌላው የሚለይበት ይመስለኛል። ይሄ ሊደገፍና ሊበረታታ ይገባል። የአጠቃላይ ምዘናው ግን አንድ ተማሪ በትምህርት ገበታው ላይ በቆየባቸው ጊዜያት ያገኛቸውን መሠረታዊ እውቀት ለመለካት የሚያገለግል ነው ስለተባለ የዲግሪው አካል ነው ማለት ነው።

 

ሰንደቅ፡- የአጠቃላይ ምዘና ፈተና መኖር ከትምህርት ጥራት መሻሻል ጋር የሚያያይዘው ነገር ይኖረዋል?


ዶ/ር አረጋ፡- ጥራት (ኳሊቲ) በአሁኑ ጊዜ ዲዛይን ላይ ያለ ነገር ነው። ውጤት (Result) ብቻ በመለካት ኳሊቲን ማረጋገጥ አይቻልም። ግብአት (Input) እና ሒደት (Process) ለትምህርት ጥራት መገኘት ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው። የመማር ማስተማር ላይ ያለው ሒደት በጥራት የተሟላ ሲሆን ውጤቱ ጥራት ያለው ይሆናል። ስለዚህ ጥራት ያለው ውጤት የግብዓትና የሂደት (Process) ድምር ውጤት ስለሆነ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል።


ፈተና አንዱን ከሌላው ለመለየት አስፈላጊ ስለሆነ የሚሰጥ ነው። ለምሳሌ የባችለር ዲግሪ ይዘህ ማስተርስ ዲግሪ ለመማር ብትፈልግ አንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመግቢያ ፈተና ይሰጣሉ። ተማሪው ለሚሳተፍባቸው የትምህርት ዓይነቶች ተገቢው መሠረት ያለው መሆኑን ለማረጋገጥ ነው። ስለዚህ ለመለየት እንዲመቻቸው ፈተና ይሰጣሉ። የተማሪውን የእውቀት ደረጃ የቱን ያህል እንደሆነ ማወቅ ጥቅም ስላለው ነው። አሁን በትምህርት ሚኒስቴር አዲስ መመሪያ መሠረት በየትኛውም በቅድመ ምረቃ የትምህርት መስክ ዲግሪ ለማግኘት አጠቃላይ የምዘና ፈተና ውሰዱ መባሉ አስቀድሞ የታወቀ ከሆነ፣ የካሪኩለም አካል ከሆነ፣ ቀደም ያለ ዝግጅት የተደረገበት ከሆነ የሚከፋ አይደለም። ከሁሉ በላይ ግንዛቤ የሚያሻው ለፈተና የቀረቡ ወጣቶች ፈተናውን ማለፍ ባይችሉ ምንድነው የሚደረገው፣ መታወቅ አለበት ቅድመ ዝግጅትም ያስፈልገዋል። ምክንያቱም ሶስት ዓመት የለፋን ወጣት ፈተና ባያልፍ በምን ዓይነት መልክ ነው መቀጠል የሚችለው። አንድ ቦታ 100ሺህ ተማሪዎች ለፈተና ቢቀርቡና የተወሰኑት ፈተና ላይ እንከን ቢኖራቸው ምንድነው የሚሆነው የሚለውን መመልከትና ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል። እንዲህ ዓይነት ክፍተቶች ቀላል ቢመስሉም ከባድ የማህበረሰብአዊ ዋጋ የሚያስከፍሉ መሆናቸው መታወቅ አለበት። አጠቃላይ ምዘና በጣም የሚፈለግባቸው የትምህርት መስኮች እንዳሉ አውቃለሁ። ለምሳሌ ጤና ላይ ተደርጓል፤ አስፈላጊ ነው። ይህን ማጠናከር ይገባል። በሁሉም የትምህርት መስኮች ላይ ምዘና ማድረግ አስፈላጊ ነው ወይ የሚለው በጥሞና መታየት አለበት።


እኔ የምደግፈው አካሄድ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲኖር ሥራዎች መከናወን ያለባቸው ከሥር ጀምሮ ነው። ከሥር በቂ ሥራ ከተሠራ ተማሪዎቹ ወደከፍተኛ ትምህርት ሲሸጋገሩም ፈተና ኖረም፣ አልኖረም የብቃት ሆኖም የጥራት ጉዳይ ጥያቄ የሚነሳበት አይሆንም።

 

ሰንደቅ፡- የመውጫ ፈተና ወስዶ ማለፍ ብቻውን የተማሪውን ብቃት ለመመስከር በቂ ነው ይላሉ?


ዶ/ር አረጋ፡- ፈተና መውሰድ ብቃትን ለማረጋገጥ በቂ መሣሪያ ነው ብለው የሚያምኑ ወገኖች አሉ። በተቃራኒው በቂ አይደለም ብለው የሚያምኑም አሉ። እኔ ፈተና አስፈላጊ ነው ሆኖም ብቻውን በቂ መለኪያ አይደለም ከሚሉት ወገን ነኝ። አንድ ሰው ከተማረ በየቀኑ በሚያሳየው መሻሻል ውጤቱን መለካት ይቻላል። ምን ያህል ጠንካራ ወይም ደካማ እንደሆነ ማወቅ ይቻላል። አንድ ተማሪ ምን ዓይነት ዕውቀት ጨብጧል ብሎ ለመመዘን የዚህ ዓይነት ፈተና ቢሰጥ ነውር የለውም። መጨረሻ ላይ በሚሰጥ ፈተና ብቻ ግን ጥራት ተረጋግጧል፣ አልተረጋገጠም ለማለት ግን አስቸጋሪ ይሆናል። ጥራት ሒደት ላይ ነው ማተኮር ያለበት። ሒደቱ (Input እና Process) ላይ የተጠናከረ ሥራ ከተሠራ ውጤቱ ጥሩ እንደሚሆን ግልፅ ነው። በቅርብ የተከፈቱ ዩኒቨርስቲዎች አሉ። ሀገራችን ባለፉት ዓመታት ከነበራት ሁለት የመንግሥት ዩኒቨርስቲ ከ40 በላይ ደርሰዋል። የግል ዘርፉ ላይ ከ100 በላይ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች አሉ። የተማሪዎች ቁጥር እጅግ ብዙ ነው። ስለሆነም ያለን የሰው ኃይል አሟጦ ለመጠቀም ፈተና የሚያልፍም የማያልፍም ለማህበረሰቡ አስተዋጽኦ የሚያደረጉበት ስትራቴጂ ከፈተናው ጋር አብሮ መታየት አለበት።

ሰንደቅ፡- የመውጫ ፈተና በቅድመ ምረቃ ሁሉም የትምህርት ዘርፎች ላይ ተግባራዊ እንዲሆን ከመወሰን ይልቅ ቀደም ሲል በሕግና በሕክምና ትምህርት መስኮች እንደተጀመረው ዓይነት በተመረጡ የትምህርት መስኮች ጀምሮ ቀስ በቀስ እያስፋፉ መሄዱ ይበልጥ ተመራጭ አይመስልዎትም?


ዶ/ር አረጋ፡- ይህ አንድ መንገድ ነው። በተመረጡ የትምህርት መስኮች ብቻ አተኩሮ እያሰፉ መሄድ የበለጠ ተመራጭ ሊሆን እንደሚችል የእኔም ሃሳብ ነው። ትምህርት ሚኒስቴርም በጤና እና በህግ ያለውን ተሞክሮ ወስዷል ብዬ አምናለሁ። ሆኖም ለሁሉም የትምህርት መስኮች የመውጫ ፈተና ማድረግ ተገቢና አስፈላጊ ነው ወይ የሚለው በጥሞና መታየት አለበት። ለምሳሌ ያህል እጅግ በጣም የተሟላ የመማር ማስተማር ተግባርን ከሚያከናውኑት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል መርጦ ‹‹በፈቃደኝነት›› የመመዘኛ ፈተና በመስጠት ውጤቱን መርምሮ ጉድለቱን አስተካክሎ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች መተግበር የተሻለ አካሄድ ሊሆን ይችላል። ከዚሁ ጋር አብሮ መታየት ያለበት መመሪያው ከመውጣቱ በፊት በቂ ውይይት፣ ምክክር ከባለድርሻ አካላት ጋር ተደርጓል ወይ ብሎ መጠየቅም ያስፈልጋል። እኔ አስከማውቀው ድረስ በግል የትምህርት ተቋማት አልተደረገም። ይህ መመሪያ ራሱ ለግሉ ዘርፍ የደረሰ አይመስለኝም።

 

ሰንደቅ፡- በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበር ፕሬዚዳንት ሆነው እንደማገልገልዎ ቀደም ሲል በሕግ እና በህክምና የትምህርት ዘርፎች ሙከራ ላይ የነበረው የመውጫ ፈተና ውጤታማ ነበር ያላሉ?


ዶ/ር አረጋ፡- በ2002 ዓ.ም ይመስለኛል፤ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥራት ላይ ችግር አለባቸው በሚል፣ እንዲያውም መዘጋት አለባቸው የሚል የውሳኔ ሃሳብ መጥቶብን እንደነበር አስታውሳለሁ። ከዚያ በኋላ ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን የትምህርት ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በጉዳዩ ላይ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ሰፊ ውይይት ተቋማቱን ከመዝጋት ይልቅ ማስተካከል ያለባቸውን ነገሮች ያስተካክሉ የሚል ውሳኔ ላይ ተደረሰ። በወቅቱ የሕግ እና የመምህራን ማሰልጠን በግል ዘርፍ እንዳይሰጥ የሚል ውሳኔም መተላለፉን አስታውሳለሁ። ሆኖም ግን እኔ እስከማውቀው ድረስ በፅሁፍ የተሰጠ ውሳኔ መኖሩን አላስታውስም። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሕግ እና መምህራን ማሰልጠን በግሉ ዘርፍ እንዲቆም ሆነ። በዚያን ወቅት ቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ መምህራንን በማሰልጠን በጣም የታወቀ ነበር። ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ደግሞ በሕግ የትምህርት ዘርፍ በጣም የታወቀ ነበር። በወቅቱ ለዩኒቲ ዩኒቨርስቲ የሕግ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ተሰጥቷቸው በሚያስደንቅ ሁኔታ እንዳለፉም አስታውሳለሁ።


በወቅቱ የታገዱት የሕግ እና የመምህራን ማሰልጠን ጉዳይ ለምን እስካሁን እንደታገዱ እንደቆዩ ወይም እንዳልተፈቀደ አላውቅም። ምናልባት ስላልጠየቅን ሊሆን ይችላል። በሀገር አቀፍ ደረጃ የመምህራን እጥረት እያስቸገረን ባለበት በዚህ ጊዜ የግል ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች መምህራንን ማሰልጠን ቢያደርጉ ጥቅም ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ። በህግ ትምህርት በጣም የተደራጁና ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው እንደዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ያሉት እንዲሰጡ ቢደረግ እንደሀገርም ጠቀሜታ ስላለው የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን ደግመው እንዲያጤኑት ማሳሰብ እወዳለሁ። መንግስት በህግና በመምህራን ማስተማር ላይ ለወሰደው ውሳኔ የራሱ ምክንያት ካለው በትምህርት ዘርፉ ያለን ባለድርሻ አካላት እንድንረዳው ቢያደርግ ጥሩ ይመስለኛል። የግሉ ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪ ፕሮግራም ለማስፋፋት፣ የፒኤችዲ ፕሮግራም ለመጀመር ቢፈልግ እንኳን በቂ የሆኑ መምህራን የሉንም። ስለዚህ በግሉ ዘርፍ መምህራን ቢሰለጥኑ ከጠቅላላው የዲግሪ ተማሪዎች 15 በመቶ የያዘው የግል የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ በይበልጥ ተጠናክሮ አወንታዊ አስተዋጽኦ ሊያደረግ ይችላል። የአጠቃላይ የብቃት ፈተና አካሄድን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ሃሳቦችን ማንሸራሸር እጅግ ይጠቅማል።

 

ያለፈው ሳምንት ዓርብ የፓርላማ የስብሰባ ውሎ በታሪክ ተመዝግቦ የሚቀመጥ ነው። የኢህአዴግ የማዕከላዊነት መርህና ጥርነፋ በኦህዴዶች ሀይለኛ ጡጫ የቀመሰበት ዕለት ነው፣ ለእኔ።

 

የሆነው ምንድንነው?


የኦሮምያ ጥቅሞች በአዲስ አበባ የሚመለከተው ረቂቅ አዋጅ ከ22 ዓመታት በሀላ አምና በዓመቱ ማሳረጊያ ገደማ በሚኒስትሮች ምክርቤት ጰድቆ ፓርላማ ደረሰ። ' ጉዳዩ በሩጫ የሚታይ አይደለም፣ በየደረጃው ሕዝብ ሊወያይበት ይገባል' ተባለና ሳይጰደቅ በይደር ለዘንድሮ ተላለፈ። ረቂቅ አዋጁም በዝርዝር እንዲፈተሽ ለህግና ፍትህ አስተዳደር ጉዳይ ቋሚ ኮምቴ እና ለቤቶችና ኮንስትራክሽን ቋሚ ኮምቴ ተመራ። ኮምቴዎቹ እንደማንኛውም አዋጅ የህዝብ ውይይት እንደሚካሄድ በቴሌቭዥን አንድ ሁለቴ አስነግረው ታህሳስ 13 ቀን 2010 የህዝብ አስተያየት ለመሰብሰብ በፓርላማው ትልቁ አዳራሽ ተሰየሙ።


የፓርላማው አዳራሽ ብዙ ሰው እንደገመተው በሕዝበ ሠራዊት አልተሞላም። በእኔ ግምት የመጣው ሕዝብ ቁጥር ከ250 እምብዛም ፈቅ የሚል አልነበረም። በዚህ ላይ ወደ 90 ከመቶ የሚገመተው ተሰብሳቢ የፓርላማ አባላት ነበሩ። እንግዲህ ይህ ሀይል ነው ሕዝብን ወክሎ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሊወያይ የነበረው።


የህግና ፍትህ ቋሚ ኮምቴ ሰብሳቢው አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት በረቂቅ አዋጁ ላይ ሀሳብ ለማሰባሰብ ስብሰባው መጠራቱን፣ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጵ/ ቤት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ አቶ ዘካርያስ ኤርካሎ የሚባሉ ሰው ጨምሮ ከአ/ አ ከተማ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሀላፊዎች መገኘታቸውን ተናገሩ።

 

ስብሰባው እንደተከፈተ የአካሄድ ጥያቄ ተነሳ። ጥያቄውን ያቀረቡት አቶ አዲሱ አረጋ የኦሮምያ ኮምኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ ነበሩ። ያሉትን ቃል በቃልም ባይሆንም ሀሳቡን ላካፍላችሁ። በረቂቅ አዋጁ ላይ ለውይይት ስብሰባ መጠራቱን ተገቢ መሆኑን ነገርግን ከ600 ሺ በላይ ሕዝባችን በኦሮምያና ሶማሌ ድንበር ላይ ተፈናቅሎ ባለበት፣ ግጭቶች ባልተረጋጉበት፣ በረቂቅ አዋጁም ላይ ሕዝቡ ባልተወያየበት ሁኔታ ረቂቁ በዚህ መልክ ለውይይት መቅረቡን አንደግፍም፣ ስብሰባው ለሌላ ጊዜ ይዛወርልን የሚል ጥያቄ አዘል አስተያየት ነበር። ተሰብሳቢው ሀሳቡ የጋራ መሆኑን ለማሳየት ይመስላል ጭብጨባው ዘለግ ያለ ነበር።


ሌሎችም ተሰብሳቢዎች 22 ዓመታት ያልተተገበረ አዋጅ በጥድፊያ ማውጣት ለምን ተፈለገ በሚል አካሄዱን ተቃውመዋል።


አቶ አባዱላ ገመዳ ስብሰባው ሲጀምር አልነበሩም፣ ተጠርተው መገኘታቸውን እሳቸውም በንግግራቸው መካከል ያመኑት ነው። አቶ አባዱላ ከምክርቤቱ የአባላትና የሥነምግባር ደንብ እና እሳቸው እንደጥቅም ካዩት ሁኔታ ጋር በማያያዝ መወያየት አለብን፣ እንዲያውም ዘግይቷል። ውይይቱ በዚህ መድረክ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፣ ሌሎች መድረኮችም ስለሚኖሩ የሚያዋጣን መወያየቱ ነው በሚል ያቀረቡት ሀሳብ በፓርላማ አባላቱ ጉምጉምታ ተቃውሞ ገጥሞታል።


ከዚያም ነገር ለማለዘብ ይመስላል ዕረፍት ተባለ። የኦህዴድ የፓርላማ አባላት ወደሀላ ቀርተው እንደገና አቋማቸውን እንዲያነሱ በእነአቶ አባዱላ ልመና ቀረሽ ውትወታ ተዥጎደጎደላቸው። (ይህኔ ነው በዕለቱ ስብሰባ ላይ ከተገኙት የፓርላማ አባላት ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት የኦህዴድ አባላት መሆናቸውን ለመታዘብ ዕድል ያገኘነው። ) ሆኖም አብዛኛው አባላት አቋማቸውን ማለዘብ አልፈለጉም። ይህ ሂደት ከአንድ ሰዓት በላይ ጊዜን ወስዶአል።


በነገራችን ላይ በረቂቅ አዋጁ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ በቴሌቭዥን ጥሪ የተጋበዘው ሕዝቡ ነበር። ነገርግን ሕዝቡ ቀርቶ አዳራሹ በፓርላማ አባላት መሞላቱ ምናልባትም ኦህዴዶች በጉዳዩ ላይ አስቀድመው ተነጋግረው አቋም ይዘው ሳይገቡ እንዳልቀረ ፍንጭ የሚሰጥ ነው።


ከዕረፍት መልስ ሰብሳቢው ሰዓቱ ከጠዋቱ 5:30 ገደማ መሆኑን በማስታወስ ስብሰባው ይቀጥል ቢባል እንኳን ጊዜ አለመኖሩን በመጥቀስ የስብሰባው ጊዜ እንዲራዘም ያቀረቡት ሀሳብ ተቀባይነት በማግኘቱ ስብሰባው ሊቋረጥ በቅቷል።


አንዳንድ ከስብሰባው ውጭ ያነጋገርኳቸው የፓርላማ ሰዎች የኦህዴድ ጥያቄ ተገቢ እንደነበር አረጋግጠውልኛል። ለዚህ የሰጡት ምክንያት ደግሞ በተለመደው የቋሚ ኮምቴዎች አሠራር አንድ ግዜ እንዲህ ዓይነት የሕዝብ ውይይት መድረክ ተጠርቶ ውይይት ከተካሄደ በሀላ እንደገና ወደታች ወርዶ ሕዝብ የሚወያይበት አሠራር እምብዛም ያልተለመደ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ በቀጥታ ለፓርላማ ቀርቦ መጽደቁ የማይቀር እንደነበር ነግረውኛል።

 

“ችግሩ በፍጥነት ካልተወገደ (አካባቢያዊ ግጭቶች)
እንደ ሐገር አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ሊጥለን የሚችል ነው”


ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ

 

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሳለፍነው እሁድ ምሽት ለመንግሥት መገናኛ ብዙሃን የመንግሥትን አቋም የሚያሳይ ወቅታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

 

በተመሳሳይ ሁኔታ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልል መንግሥታት በተለይም በምዕራብ ሐረርጌ በድሮሎቢ ወረዳ በጋድሌ ቀበሌ የተፈፀመውን አሳዛኝ ጥቃት በተመለከተ ያወጡት መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል።

 

*** *** ***

 

የተከበራችሁ የአገራችን ሕዝቦች፤ በቅርቡ በተለያዩ የሐገራችን አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የሐገራችንን ሰላም እና መረጋጋት የሚያውኩ ችግሮች ታይተዋል። በተከሰቱት ግጭቶች ምክንያት የሰው ህይወት ጠፍቷል። ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል። የህዝብ ሐብት እና ንብረት ወድሟል። እጅግ የምሳሳለትን የሰላም፤ የልማት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሥራችንን የሚጎዱ ችግሮች ተከስተዋል። በተለይም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት መከሰቱ ይታወቃል።


የፈዴራል መንግሥት ከሁለቱ የክልል መንግሥታት ጋር በቅርበት በመሥራት ችግሩ እንዲቀረፍ ያለሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ጉዳዩ እልባት ወደ ሚያገኝበት ምዕራፍ በመሸጋገር ላይ ነበር። ሆኖም በቅርቡ ግጭቱ እንደገና ያገረሸ ሲሆን በንጹሀን ዜጎቻችን ላይ የሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የሐብትና ንብረት ውድመት በማስከተል ላይ ይገኛል።


በምዕራብ ሐረርጌ በድሮሎቢ ወረዳ በጋድሌ ቀበሌ ለደህንነታቸው ሲባል በአካባቢው በአቅራቢያ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ተጠልለው በነበሩ የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች የጅምላ ግዲያ ተፈጽሞባቸዋል። በራሴና በፌዴራል መንግሥት ስም በንጹሐን ዜጎች ላይ በደረሰው አዳጋ የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን እየገለጽኩ ለተጎጅዎቹ ቤተሰቦች፣ ዘመድ አዝማድና ለመላው የአገራችን ህዝቦች መጽናናትን እመኛለሁ።


መንግሥት ድርጊቱን እያወገዘ ጉዳዩን የሚያጣራ ግብረ ኃይል ያቋቋመ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ። የማጣራቱ ሂደት እንደተጠናቀቀም አስፈላጊውን እርምጃ የሚወሰድ ሲሆን የማጣራት ሂደቱን ውጤት ለሕዝቡ በዝርዝር እንደምንገልጽ ከወዲሁ ለማሳወቅ እፈልጋለሁ። በተመሳሳይም በጨለንቆና ሌሎች አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ በአካባቢው በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ የሞትና የመቁሰል አደጋ አጋጥሟል።


በድጋሚ በመንግሥትና በራሴ ስም በዜጎቻችን ህልፈተ ሕይወት ምክንያት የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን እየገለጽኩ ለተጎጂዎቹ ቤተሰቦች፣ ዘመድ አዝማድና ለመላ የአገራችን ህዝቦች መጽናናትን እመኛለሁ። የጸጥታ ኃይሎቻችን መንግሥት ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ሰላምን እንዲያረጋግጡ ተልዕኮ ሰጥቷቸው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። የጨለንቆን ግጭት ጨምሮ ተልዕኳቸውን እየፈጸሙ ባሉበት ወቅት ያጋጠሙ ክፍተቶች ካሉ አሰራሩን ተከትሎ መንግሥት የሚጣራ ሲሆን የማጣራቱ ሂደት እንደተጠናቀቀም ውጤቱን ለሕዝቡ በዝርዝር ይፋ የምናደርግ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ።


በተጨማሪም በአማራ፣ በትግራይ እና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ አንዳንድ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፤ እንዲሁም በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ክቡር የሰው ህይወት መጥፋቱ፤ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸው እና የዜጎች ሐብት እና ንብረት መውደሙ ብቻ ሳይሆን፤ ችግሩ በፍጥነት ካልተወገደ እንደ ሐገር አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ሊጥለን የሚችል ነው።


በመሆኑም፤ በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በቦረና፣ በጉጂና በባሌ የተለያዩ አካባቢዎች እና በቅርቡም ጨለንቆ አካባቢ በተከሰተው ግጭት፤ እንዲሁም በአዲግራት፣ በወለጋ፣ በደብረ ታቦር፣ በወልድያ፣ በባህርዳር፣ በጎንደር እና በአምቦ ዩኒቨርስቲዎች በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ በተማሪዎች የአካል ጉዳት መድረሱ እና በአንዳንዶቹም የሰው ህይወት መጥፋቱ በእጅጉ አሳዛኝ ነው። በዚህ አጋጣሚ ህይወታቸውን ባጡ ተማሪዎች የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን እየገለጽኩ ለተማሪ ወላጆችም መጽናናትን እመኛለሁ።


ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ትምህርትን በፍትሐዊነት ለማዳረስ እና የተማሩ ዜጎችን ቁጥር ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከ50 በላይ ዩኒቨርስቲዎች ተገንብተው፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተው ትምህርታቸውን መከታተል የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እነዚህ የሐገር ተስፋ ተደርገው የሚታዩ የትምህርት ተቋማት የሚታዩ አስተዳደራዊ ችግሮችን እና ተማሪዎች የሚያነሷቸውን ሌሎች ችግሮችን በማዳመጥ መፍትሔ ለማስቀመጥ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል።


በአሁኑ ወቅት በተጠቀሱት ዩኒቨርስቲዎች ተከስቶ የነበረው ችግር የክልል እና የፌዴራል መንግስታት፤ እንዲሁም የየዩኒቨርስቲዎች አመራሮች እና የየአካባቢው የመስተዳድር አካላት፤ ከተማሪዎች፣ ከሐገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት መሪዎች እና የጸጥታ አካላትን ባሳተፈ ሁኔታ ችግሩ ተወግዶ፤ ሁኔታዎች ተረጋግተው የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል ለማድረግ ተችሏል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተፈጠረውን ይህን ችግር ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል። ችግር በተፈጠረባቸው የትምህርት ተቋማት በተማሪዎች ዘንድ የተፈጠረውን የደህንነት ሥጋት ለማስወገድ እና ለመማር ማስተማሩ ሂደት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በተቋማቱ የሰዓት እላፊ ገደብ እንዲኖር፣ የተቋማቱን ሰላም ለማስከበር የጸጥታ ኃይሎች ጥበቃ እንዲኖር ተደርጓል።


በአጠቃላይ በክፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የጸጥታ መደፍረስ ችግር አንዳይኖር፤ የዜጎች ህይወት ዋስትና እንዲያገኝ እና በዜጎች ሐብት እና ንብረት ላይ የሚደርስ ውድመት እንዳይኖር ለማድረግ አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል።


በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስት አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰቱት ግጭቶች የሰላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ትግላችንን የሚጎዱ፤ ሐገረችንን ወዳልተፈለገ አለመረጋጋት ውስጥ የሚከቱ እና በመራራ ትግል የተገኘውን ብሩህ ተስፋ የሚያጨናግፉ ክስተቶች ናቸው። ለዘመናት የቆየ የአብሮ መኖር እሴቶቻችን የሚጎዱ ችግሮች በመሆናቸው መንግስት ከሕዝቡ ጋር በመሆን ችግሮቹን በማያዳግም ሁኔታ ለመፍታት በቁርጠኝነት ይሰራል።


ለዘመናት በድህነት የኖረውን ህዝባችንን ከድህነት አረንቋ ለማውጣት እና ከኋላ ቀርነት ለማለቀቅ፤ እንዲሁም የሰላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጥረታችን ለማጠናከር በማሰብ፤ በከፍተኛ ወጪ በተለያዩ የሐገሪቱ አካባቢዎች የተገነቡት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ የሐገራችንን ህዝብ ችግር ለመፍታት በጥናት እና ምርምር ዘርፍ ተሰልፈው የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ ታስበው ከፍተኛ ገንዘብ ፈሶባቸው የተቋቋሙ ናቸው።


በመሆኑም በእነዚህ ተቋማት ገብተው የሚማሩ እና ሐገሪቱ በከፍተኛ ተስፋ የምትጠብቃቸው ተማሪዎች ምክንያታዊ አስተሳሰብን በመከተል፣ ከግጭት በመራቅ ለሐገራቸው ተስፋ ይሆኑ ዘንድ ለትምህርታቸው ልዩ ትኩረት ሰጥተው ጠንክረው መማር ይኖርባቸዋል። በሌላ በኩል፤ መረጃን በማሰራጨት ተግባር የተሰማሩ የተለያዩ አካላት የሚያሰራጯቸውን መረጃዎች ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት መስጠት እና በኃላፊነት መንፈስ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።


በተጨማሪም ህዝቡ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች የሚያገኛቸውን መረጃዎች ትክክለኛነት ለማረጋገጥና መረጃዎቹን በተለያየ አግባብ ለማጣራት የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በመደበኛው የሚዲያ ዘርፍም ሆነ በሌሎች የመረጃ ማሰራጫ አግባቦች በመጠቀም መረጃን የሚያሰራጩ ተቋማት ህግን አክብረው ሊንቀሳቀሱ ይገባል።


ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በመደበኛው የሚዲያ ዘርፍም ሆነ በሌሎች የመረጃ ማሰራጫ አግባቦች በመጠቀም መረጃን የሚያሰራጩ ተቋማት ህግን አክብረው ሊንቀሳቀሱ ይገባል። ሐሰተኛ እና የተጋነኑ መረጃዎችን በማሰራጨት የህዝቡን ሰላም፣ ደህንነት እና አኩሪ የአብሮ መኖር እሴቶች የሚንዱ እና ህግን በሚያስተላልፉ የግልም ሆነ የህዝብ የመገናኛ ብዙሃን ከዚህ መሰል ተግባራት መራቅ ይኖርባቸዋል። መንግስት እንዲህ ያሉ ችግሮችን በሚፈጽሙት ላይ ተከታትሎ እርምጃ የሚወስድ መሆኑም በግልጽ መታወቅ ይኖርበታል።


የኢፌዴሪ መንግሥትና ገዢው ፓርቲ በአገራችን በተለያዩ ቦታዎች እያጋጠሙ ያሉትን ግጭቶች መሰረታዊ መንስኤን በመለየት ችግሩን ከሥር መሰረቱ የሚፈታ እርምጃ የሚወስድ ሲሆን መላ የአገራችን ሕዝቦችም እንደ ወትሮው ከመንግሥት ጎን በመቆም ያልተቆጠበ ድጋፋችሁን እንዲትቸሩን በመንግሥትና በራሴ ስም ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። በተለይም ግጭቱ በሚከሰትባቸው የኦሮሚያና የኢትዮጰያ ሶማሌ ክልል ነዋሪ የሆኑት ወንድማማች ሕዝቦች ለሰላምና ለወንድማማችነት ቅድሚያ በመስጠትና ለግጭት ጥሪዎች ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት በጋራ በመንቀሳቀስ ሰላማቸውን እንዲያስከብሩ በኢፌዴሪ መንግሥት ስም ጥሪዬን እያቀረብኩ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት በቅንጅት ችግሩን ለመቅረፍ በመረባረብ ላይ ይገኛሉ።


በድጋሚ በተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠሙ ግጭቶች ሳቢያ በዜጎቻችን ላይ በደረሰው የሞት አደጋ የተሰማኝን መራር ሐዘን እየገለጽኩ፣ ለመላ ቤተሰቦቻቸው፣ ዘመድ አዝማዶቻቸውና ለአገራችን ሕዝቦች መጽናናትን እመኛለሁ።

 

*** *** ***


የኦሮምያ ክልል


ምእራብ ሀረርጌ ዞን ሀዊ ጉዲና እና ዳሮ ለቡ ወረዳዎች የሶማሌ ወንድሞቻችንን የማይወክሉ ታጣቂዎች ሰላማዊዉን ማህበረሰብ ተገን አድርገዉ ከአካባቢዉ እየተነሱ ኢብሳ እና ታኦ በሚባሉ ቀበሌዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም ከታህሳስ 5 እስከ ዛሬዉ ዕለት (እሁድ ታህሳስ 8 ቀን 2010 ዓ.ም) በተጠቀሱት ቀበሌዎች 29 የኦሮሞ ተወላጆች ሞተዋል። ከ360 በላይ መኖሪያ ቤቶችም ከነሙሉ ንብረታቸው ወድመዋል።


በሃዊ ጉዲና ወረዳ በተፈጠረዉ ግጭት የወንድሙን አቶ አህመድ ጠሃን ሞት የተረዳዉ አቶ ዚያድ በከፍተኛ የሀዘን ስሜት በመሆን ግብረአበሮቹን በማስተባባር ሃዊ ጉዲና ወረዳ ላይ ከተፈጠረዉ ግጭት ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸዉ በጋዱሎ ቀበሌ ነዋሪ በሆኑ ንፁሃን የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተወላጅ ወንድም እና እህቶቻችን ላይ ዘግናኝ እርምጃ ይወስዳል። እስካሁን በደረሰን ሪፖርትም በጋዱሎ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ የ32 የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች ህይወት ማለፉን አረጋግጠናል።


የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ሀዊ ጉዲና እና ዳሮ ለቡ ወረዳዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ በደረስዉ ጉዳት የተሰማዉን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ህይወታችዉን ላጡ ዜጎች ቤተስቦች እና ወዳጆች መፅናናትን ይመኛል። የተፈፀመዉን ጥቃትንም አጥብቆ ያወግዛል። ጥፋተኞችንም በህግ ቁጥጥር ስር አዉሎ ለፍርድ ለማቅረብ በመስራት ላይ ይገኛል።


በሃዊ ጉዲና እና በዳሮ ለቡ የተፈጠሩ ዘግናኝ ጥፋቶች ማንኛዉንም ህዝብ አይወክሉም። ስለሆነም በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ሁሉም ብሄር ብሄረስቦች እንደተለመደዉ አብሮነታችዉን አጠናክረዉ ሰላማዊ ኑሮአቸዉን እንዲቀጥሉ ጥሪዉን ያስተላልፋል። የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደዚህ አይነት ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ ለማድረግ ጠንክሮ በመስራት ላይ ይገኛል።

 

*** *** ***

 

ሶማሌ ክልል


በምእራብ ሀረርጌ ዞን፣ ዳሩ ለቡ ወረዳ፣ ጋዱላ ቀበሌ በግፍ ህይወታቸውን ላጡ የሶማሌ ክልል ተወላጅ ዜጎች ከክልሉ ፕሬዚዳንት ክቡር አብዲ ማህሙድ ዑመር የተላለፈ_የሐዘን_መግለጫ

 

*** *** ***

 

ለመላው የሀገራችን ህዝቦች፣ ለመላው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝብ በተለይ በግፍ ህይወታቸው ላጡ ቤተሰቦች በራሴና በክልሉ መንግስት ስም የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን ለመግለጽ እወዳለሁ::


በሀገራችን የተጀመረውን የልማትና የዴሞክራሲ ጎዳና እክል ለመፍጠር እንዲሁም የፌደራል ሥርዓቱን ለመገርሰስ ሌት ተቀን የሚተጉት ሀይሎች በፈጠሩት የዘር ጭፍጨፋ ጥቃት ታህሳስ 6 ቀን 2010 ዓ.ም በምእራብ ሀረርጌ በዳሩ ለቡ ወረዳ ጋዱላ ቀበሌ ለደህንነታቸው ሲባል በአካባቢው በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ የተጠለሉ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተወላጆች ላይ በደረሰው የጅምላ ጭፍጨፋ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች የተሰማን ሐዘን ጥልቅ ሲሆን ፤ ይህንን ጥቃት የፈጸሙት ግለሰቦችን ወደሕግ ለማቅረብ የክልላችን መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የሚሰራ መሆኑን ላሳውቅ እወዳለሁ::


የክልላችን መንግሥት ይህንን ጥቃት የፈጸሙ አካላትን በጅምላ አይፈርጅም ወይም ጥቃት አድራሾቹ መላ የኦሮሞን ህዝብ ይወክላሉ ብለንም አናምንም:: ይህንን የፈጸሙት ጥቂት የጥፋት ሀይሎች ናቸው ብለን እናምናለን። የክልላችን መንግሥትና ህዝብ ሰላምና ልማት ፈላጊ ነው። በዋናነት ህዝባችንን ከድህነት ለማላቀቅ ቀንደኛ ጠላት የሆነው ድህነት ጋር የጀመርነውን ትግል አጥናክረን በመቀጠል የህዝባችንን ህይወት የሚሻሻልበት መንገድ ለመስራት ሰላም ትልቅ ግብአት መሆኑን ጠንቅቀን ስለምውቅ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ለሠላም ትልቅ ዋጋ እንከፍላለን።


በመጨረሻም መላው የክልላችን ህዝቦች ከበቀል በጸዳ አስተሳሰብ የተጀመረውን የሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች የሰላም ተግባር አጠናክረው በማስቀጠል ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው የመመለስ ስራም ሳይስተጓጎል የሁለቱ ክልሎች የሰላም ጥረትን እንዲጠናከር መልእክቴን እያስተላለፍኩ በተለያዩ የሀገራችን ቦታዎች ህይወታቸውን ላጡ የሀገራችን ዜጎች በሙሉ ነብስ ይማር እላለሁ፤ አመሰግናለሁ::


አብዲ መሀሙድ ዑመር
የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት
ታህሳስ 9 ቀን 2010 ዓ.ም
ጂግጂጋ 

 

ብቸኛው- ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ

‹‹እንቧለሌ››
(1) ቅድመ-ነገር፡- የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ጋዜጠኛ እና የማህበራዊ ሚዲያ ንቁ ተሳታፊ የሆነው ጋዜጠኛ የሺሀሳብ አበራ ‹‹እንቧለሌ›› የሚል መጽሃፍ አሳትሞ ባለፈው ሳምንት ገበያ ላይ ውሏል። ጋዜጠኛው የአማራ ርብሄርተኝነት አቀንቃኝ፣ ብዙ ተከታይ ያለው፣ የመንግስት ጋዜጠኛ እና ወጣት በመሆኑ የተነሳ በእሱ በኩል የአማራ ወጣቶችን የፖለቲካ አረዳድ፣ አቋም እና አፈታትለማወቅ እንደሚረዳኝ በማመን ‹‹እንቧለሌ››ን ተሽቀዳድሜ አነበብኳት። በጠቅላላ አነጋገር ሙሉ በሙሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የያዘች የወግ መጽሃፍ ናት ማለት እችላለሁ። በመጽሃፉ ብዙ ገጾች እና ታሪኮች ላይ የአማራ ብሄርተኝነትን ትዳስሳለች። ትኩረቴን የሳበኝ እና ለዚህች አጭር ጽሁፍ መነሻ የሆነኝን ታሪክ ያገኘሁት ቅማንት እንደ ክሪሚያ የተመሰለችበት የወግ ክፍል ነው። የዚህ ጽሁፌ ዓላማ በመጽሃፉ ላይ ሙሉ ዳሰሳ ማቅረብ አይደለም። የቅማንትን ነጠላ-ታሪክ እና የእንቧለሌን የብሄር ብያኔ መነሻ በማድረግ አማራነት ምንድነው?የሚል ውይይት፣ ክርክርና ሙግት መክፈት ነው።


(2) ቅማንት በመጀመሪያ በአማራ ክልል ምክር ቤት ይሁንታ እና በኋላ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስፈጻሚነት በተደረገ ህዝበ-ውሳኔ አንድ ቀበሌ ተጨምሮለት ‹‹ብሄረሰብ›› መሆኑ ታውቆለት የራሱን አስተዳደር እንዲመሰርት ተፈቅዷል።

 

መግቢያ፣


የማህበራዊ ሳይንስ ጽንሰ-ሃሳቦች ተበይነው ያለቁ አይደሉም። ብሄርተኝነት በስተቀር አይደለም። ከስም አጠራሩ ጀምሮ በምን ማለትነቱ ላይ ስምምነት የለም። ስምምነት የለም ማለት አንድ ዓይነት አረዳድ የለም ማለት እንጅ ብሄርተኝነት አይታወቅም፤ እንግዳ ነገር ነው ማለት ከቶ አይደለም። የአማራ ብሄርተኝነት ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በመቀንቀን ላይ ነው። ብሄርተኝነት ቀለመ-ብዙ መሆኑ የአማራ ብሄርተኝነት በተለይ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ካለው ተመሳስሎሽ ጋር ተደምሮ የአማራ ብሄርተኝነት ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ የተቆረጠ መልስ መስጠትን አስቸጋሪ አድርጎታል። የአማራ ብሄርተኝነትን መነሻ፣ የመሄጃ መንገዶች እና መድረሻውን ለይቶ ለማወቅ በቅድሚያ የብሄርተኝነቱን ወርድና ስፋት የሚወስነውን ምን ማለትነቱን መበየን አስፈላጊ ይሆናል።


ብሄር ምንድነው?ብሄር የአንድ ሰው ተፈጥሯዊ ዘር ነው የሚሉ (Primoridialist Theory)፤ የስልጣን መያዣ ኤሊት-ሰራሽ የፖለቲካ መሳሪያ ነው የሚሉ (Instrumentalist View) እና የጊዜና የሁኔታዎች ሂደት ውጤት የሆነ ማህበረሰባዊ ስሪት ነው የሚሉ (Socially Constructed) የዘርፉ ምሁራን የከረመ ሙግት አላቸው። እነዚህ ብሄርን ማን ሰራው የሚል ጥያቄን በመመለስ የብሄርን ምን መሆን የመመለስ ሙከራ የሚመዝዛቸው ክሮች ናቸው። አንድ ማህበረሰብ ብሄር የሚሆነው ምን ምን ቅድመ-ሁኔታዎችን ሲያሟላ ነው?ብሄርን የሚያቋቁሙ መስፈርቶች ምንድን ናቸው? የሚለውን ስንጠይቅ ቋንቋ፣ ባህል፣ ስነ-ልቦና፣ መልክዓ-ምድር ወዘተ ሆነው እናገኛለን።


ብሄርን የሚያቋቁሙ ቅድመ-ሁኔታዎች ሆነው የተቀመጡት መስፈርቶች በብሄር ውስጥ ያላቸው ድርሻ (የሚያቀብሉት አበርክቶ) ምን ያህል እንደሆነ በህግም ሆነ በአካዳሚያዊ (የምርምር) ጽሁፎች ተወስኖ አይገኝም። እነዚህ መስፈርቶች በጣምራነት (Cumulative) መሟላት ያለባቸው ወይም በአማራጭነት ሊተካኩ የሚችሉ (Optional) ስለመሆናቸውም እንዲሁ። እነዚህ መስፈርቶች ‹ሰብጀክቲቭ› የሆነውን የብሄር ማንነት ‹ኦብጀክቲቭ› የሆነ መስፈሪያ የማበጀት ሙከራዎች ናቸው። ከዚህ በቀር ለሁሉም ብሄሮች በተመሳሳይ ድርሻ እና ተጽዕኖ (ማዋጣት) ሊያገለግሉ አይችሉም። የአማራ ብሄርተኝነት በእነዚህ መስፈርቶች ተሰፍሮ የሚያልፍ መሆኑ የማያከራክር ቢሆንም የመስፈርቶቹ ድርሻና ተጽዕኖ ምን ያህል እንደሆነ መገምገም የብሄርተኝነቱን ተፈጥሮ እና መጠነ-ዙሪያ ለመቀንበብ ያገለግላል።

 

የቅማንት ነገር፣


የቅማንትን የብሄር ጥያቄ በመጀመሪያ ወደ አደባባይ ይዘው የወጡት አቶ ነጋ ጌጤ ቅዳሜ ሃምሌ 12 ቀን 2006 ዓ.ም ለወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ፤ ‹‹የቅማንት ብሄረሰብ ቀደምት ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነው።


መገለጫው በእኛ በቅማንቶች አባት፣ እሚታ፣ አያት፣ ቅድመ-አያት- ቅማንት- ምንዥላት- እንጃላት ብለን 7ኛ ቤት ድረስ ይሄዳል። 6ኛው ዙር ምንዥላት የሚባለው አሁን ጠፍቷል። አሁን ያለው የመጨረሻው ቅማንት ነው። እነዚህ ከአባት ተጀምሮ ወደ ላይ የሚጠሩት የዘር ተዋረዶች ናቸው። …ኖህ ሶስት ልጆች አሏቸው- ሴም፣ ያፌት፣ ካም ይባላሉ። አፍሪካውያን የካም ልጆች ናቸው። ከዚህ መሃል የእኛን ዘር የምናወጣውከከነአን ልጆች ነው። አራዲዮን-አደረኪን ወለደ። አደረስኪ ሶስት ሚስቶችን አገቡ። አንደኛዋ ሚስታቸው አንዛኩና ትባላለች። ከአንዛኩና ቅማንት….ይወለዳሉ።…›› ይላሉ። ይህ የአቶ ነጋ ጌጤ ትርክት ብሄር በቀጥታ የዘር ቆጠራ እንደሆነ የሚነግረን ነው። የአቶ ነጋ ጌጤ የዘር ቆጠራ የሚያነሱትን የብሄር ማንነት ይገባናል ጥያቄ የሚደግፍ አይሆንም። በህገ-መንግስቱ ዘር የብሄር ማንነትን የሚያስገኝ መስፈርት ሆኖ አልተደነገገም። ብሄርን በዘር የወደኋላ ቆጠራ ለማግኘት የሚደረግ ጉዞ ማረፊያው የአማራ እና የኦሮሞ ብሄሮችን ከአንድ ዘር የተገኙ ናቸው ወይም የሰው ሁሉ ዘር አንድ ነው ወይም በተለይ አማራ የሚባል ብሄር የለም የሚል ይሆናል። ስለሆነም እገሌ እንቶኔን ወለደ ዓይነት የብሄርተኝነት ትርክት ብሄርተኝነትን የሚንድ እና ትርጉም የማይሰጥ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባለ በደምና በአጥንት በተዋሃደ ህዝብ መካከል ዘርን ተከትሎ አንዱን ከሌላው ለመለየት መሞከር የሚቻል አይደለም። ብሄርተኝነትንም ከፖለቲካ ርዕዮትነት አውርዶ የለየለት ዘረኝነት ያደርገዋል። አንድ ማህበረሰብ ብሄር ለመሆን የተለየ ዘሩን እንዲቆጥር የሚያስገድድ የህግም ሆነ የማህበራዊ ስምምነት በሌለበት ሁኔታ አቶ ነጋ ጌጤ የቅማንትን ራሱን የቻለ የተለየ ብሄር መሆኑን ለማስረዳት እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ ዘር የመቁጠራቸው ተጠየቅ ግልጽ አይደለም። ባህል፣ ቋንቋ፣ ስነ-ልቦ­ና፣ መልክዓምድር… የሚሉት ቅድመ-ሁኔታዎች ቅማንትን ከጎንደሬው የማይለዩት ስለሆነ ልዩነትን ፍለጋ ይመስላል።


ቅማንት በአሁኑ ጊዜ የብሄር እውቅና ተሰጥቶት የራሱን አስተዳደር አቋቁሟል። እውቅና የተሰጠው ግን በየትኞቹ መስፈርቶች ተመዝኖ እና ምን ምን አሟልቶ በመገኘቱ እንደሆነ ግልጽ አይደለም። በአማራ እና በቅማንት መካከል ያለውን አንድ መሆን እና ያው ራስነት ስናይ የቅማንት ብሄርተኝነት ልሂቅ-ሰራሽ የፖለቲካ መሳሪያ እንጅ መሬት ያለ የሚጨበጥ ማህበረሰባዊ መሰረት ያለው አይመስልም። የቅማንት ማንነት መነሻው ምንም ቢሆን መድረሻው ራስን በራስ የማስተዳደር እና እውቅና የማግኘት እንደ አገውነት፣ አርጎባነት…ወዘተ እስከሆነ ድረስ የሚፈጥረው የኀልዮትም ይሁን የተግባር መፋለስ አይኖርም።


ይህን ነጥብ በዝርዝር ከማየታችን በፊት ብሄርተኝነት ይልቁንም አማራነት በ‹‹እንቧለሌ›› የተገለጠበትን ዓይነት እንመልከት። ‹‹አማራነት ስነ-ልቦናዊ ስሜት እንጅ የዘር እና የቋንቋ ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ አምነናል። ሙስሊሙም ክርስቲያኑም፣ ቅማንቱም፣ አገውም…የራሱን ልዩ የሚያደርገውን ባህል እንደያዘ በትልቁ ሲሰፋ የአማራ ማንነትን ይዞ ኢትዮጵያዊነትን ያፈካል። ደግሞ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ዘር የሚባል ባዮሎጅ የለም። አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ…የሚል ዘረ-መል በህክምና አታገኝም። …ብሄር በፖለቲካ የሚፈጠር ማህበራዊ ውህደት ያለው የነገድ መጠሪያ ነው። …ብሄር የሚባለውም የደም ጉዳይ ሳይሆን የጋራ ስነ-ልቦና የሚፈጥረው የህዝብ ጉባዔ ነው።›› ገጽ 79።


ይህን የምትለን በእንቧለሌ የፖለቲካዊ ወጎች መጽሃፍ ላይ የቅማንት አማራ ሆና የተሳለችው እና በሙያዋ የስነ-ማህበረሰብ እና የታሪክ ተመራማሪ እና አዝማሪ መሆኗን የምትነግረን ዶ/ር አበበች ደሴ ናት። ‹‹እኔ እንደ ቅማንት ከአማራው የሚነጠል ማንነት የለኝም።…አንጓው ቢለያይም ሸንበቆው አንድ ነው›› (ገጽ 78) በማለትም የቅማንትን አማራነት ታረጋግጣለች። ‹‹እንቧለሌ›› እንዲህ ያሉ ስስ እና ግዙፍ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በልቦለድ፣ ከልቦለድም በወግ መልኩ በማቅረቡ፣ ከማቅረቡም በላይ ርዕሰ-ነገሩን በሚገባ መንተንተን እና በዝርዝር መዳሰስ ባለመቻሉ (ባለመፈለጉ) ክብደት ተሰጥቶት በምንጭነት ለመጥቀስ የማይመች መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በጠቅላላ አነጋገር ብሄር ‹የዘር ቆጠራ አይደለም፤ በጊዜ እና በሁኔታዎች ሂደት ውስጥ የተፈጠረ የአንድ ህዝብ የጋራ ስነ-ልቦና ነው። ስለሆነም ቅማንት ዘሩን እንዴትም እና ወደየትም ቢቆጥር አማራ ነው› የሚል ጭብጥ ይዞ ይሟገታል። ለአቶ ነጋ ጌጤ በተለይ የተጻፈም ባይሆን የሁለቱ የብሄር ብያኔ የቀጥታ ተቃራኒ ነው።
የአቶ ነጋን የብሄር ትርጓሜ እና አረዳድ ከተቀበልን ቅማንትና አማራ ሁለት የተለያዩ ብሄሮች ይሆናሉ። ‹‹እንቧለሌ›› ደግሞ ቅማንትም እንደ አገው አማራ ነው በማለት ቅማንትን በአማራነት ውስጥ እንዳለ አንድ ንዑስ ማንነነት አድርጎ ያቀርበዋል። ‹‹እንቧለሌ›› በአንድ በኩል‹‹አማራነት ስነ-ልቦናዊ ስሜት›› ነው ቢልም አጥንትና ደም ቆጠራ ጭምር መሆኑን እንደሚቀበል በተዘዋዋሪ ‹‹…የዘር እና የቋንቋ ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ…›› በማለት ይነግረናል። ጥቂት ዝቅ ብሎ ደግሞ ‹‹…ብሄር የሚባለውም የደም ጉዳይ ሳይሆን የጋራ ስነ-ልቦና የሚፈጥረው የህዝብ ጉባዔ ነው።›› በማለት ብሄርን በዘር ቆጠራ ለማቆም መሞከርን እንደማይስማማበት ይጠቁማል። ደራሲው ዘር እንደ ባህል፣ እንደ ቋንቋ ወዘተ ሁሉ የብሄር ማንነት አንድ አምድ ሆኖ መቆሙን የሚቀበል ይሁን ወይም ዘር በብሄር ማንነት ውስጥ ድርሻ የለውም እንደሚል እርግጠኛ ሆኖ መናገር ያስቸግራል። ይህ ግራ መጋባት እና ግራ አጋቢነት የደራሲው ብቻ ሳይሆን የአማራ ብሄርተኝነት አቀንቃኞች ሁሉ ይመስላል። ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የስበት ማዕከል ሆኖ የቀጠለው አማራ ብሄርተኝነት የብሄርተኝነቱን መጠነ-ስፋት መወሰንና ማሳወቅ አልቻለም። ይህ ክፍትነቱ አማራው ለኢትዮጵያዊነት ካለው ቀናኢነት ጋር ተደምሮ የአማራብሄርተኝነት በአንድነት ኃይሉ የሚወሰድ ያደርገዋል። ይህ የደራሲው ከሁሉም ልሁን ማለት የብሄርተኝነቱን ዥዋዥዌ የሚጠቁም ነው ሊባል ይችላል። እነዚህን ሁለት የብሄር አረዳዶች እና አፈታታቸውን ይዘን የዚህ ጽሁፍ ዋና ጭብጥ የሚያርፍበትን ጨመቅ እንጠይቅ። ቅማንት አማራ ነው ወይ?የአማራ ብሄርተኝነት ከአጥንትና ደም ቆጠራ ያመለጠ የስነ-ልቦና አንድነት ነው።አለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ ‹‹የጎጃም ዘር በሙሉ ከአባይ እስከ አባይ›› በሚለው መጽሃፋቸው የጎጃምን ዘር እገሌ እንቶኔን ወለደ በሚለውተለምዷዊ የዘር ቆጠራ የጎጃምን ማን መሆንና ኬት መጣነት አብራርተዋል። በእንዲህ ያለው የህዝቦች ድልድል በጎጃምና በቅማንት መካከል ያለው ልዩነት፣ በአገውና በወሎ መካከል እንዳለው ያለ ልዩነት ይሆናል። በዚህ የዘርን ቆጥሮ ማንነትን የመወሰን የብሄርነት አበያየን ወሎም፣ ሸዋም፣ ጎንደርም፣ ጎጃምም ራሳቸውን የቻሉ የተለዩ ህዝቦች ይሆናሉ። እንዲህ ከሆነ አማራ ማን ነው?ወይስ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ-ማርያም እንደሚሉት አማራ የሚባል ብሄር የለም?

 

ድህረ-ነገር/መደምደሚያ፡-


በዚህ ጸሃፊ እምነት ማንነት በይበልጥ ስነ-ልቦና ነው። ብሄርን ከሚያቋቁሙ መስፈርቶች ውስጥ የጋራ ስነ-ልቦና እጅግ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። በቁጥር ይሄን ያህል ብሎ በሂሳባዊ ስሌት ለመግለጽ ቢያስቸግርም የአንበሳውን ድርሻ ያህል ወይም ከዚያም የበለጠውን ያህል ወሳኝነት አለው። የኦሮሞም ሆነ የትግሬ ብሄርተኝነት የቆመው እኔ ኦሮሞ ነኝ፣ እኔ ትግሬ ነኝ በሚል ችካል ላይ እንጅ እገሌ እንቶኔን ወለደ በሚል ስሌት አይደለም። ማንነት ስሜት እንጅ ስሌት አይደለም። አማራነት ህዝቦች የሚጋሩት የጋራ ስነ-ልቦና እንጅ አጥንትና ደም ቆጠራ አይደለም። አማራነት በጊዜና በሁኔታዎች የረጅም ጊዜ ሂደት የተፈጠረ አንድ የጋራ ስነ-ልቦና ነው። ይህ ምን ማለት ነው? ቅማንቱንም፣ አገውንም፣ ጎጃሜውንም፣ ጎንደሬውንም…ወዘተ እኩል አማራ የሚያደርግ በመካከላቸው ያለውን ንዑስ ልዩነቶች የሚያስረሳ የጋራ ስነ-ልቦና አላቸው ማለት ነው። ይህ የአማራ የጋራ ስነ-ልቦና ራሱ ምንድነው? የአንድ ህዝብ ስነ-ልቦና በተለያዩ መሰረቶች ላይ ሊቆም ይችላል። የሚያስተሳስራቸውን የጋራ ገመድ በጊዜ እና በሁኔታዎች ሂደት ይፈትላሉ። የእኛ ነው በሚሉት ወይም የእነሱ ነው በሚባል አንድ ወይም ብዙ መሆኖች ላይ ሊመሰረት ይችላል። የቅማንትም ሆነ የመንዝ፣ የብቸናም ሆነ የቋራ፣ የጋይንትም ሆነ የሳይንት፣ የአገውም ሆነ የወልቃይት አማራ እኩል የሚጋራው የጋራ መገለጫው ትምክህተኝነት እና ነፍጠኝነቱ ነው። የአማራ ሁሉ የጋራ ስነ-ልቦናው መሰረቱ ትምክህቱ እና ነፍጠኝነቱ ነው። የተቀሩት ሌሎች ሁሉ አማራውን ያለ ልዩነት ትምክህተኛ እና ነፍጠኛ ነው ይሉታል። ይህ ማለት ግን አማራው ከትምክህተኝነቱ እና ነፍጠኝነቱ በቀር የሚጋራው የጋራ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ… ወዘተ የለም ማለት አይደለም። የስነ-ልቦና አንድነቱ የተሸመኑበትን ዋና ድርና ማጎች ለመለየት ብቻ ነው። አማራው ራሱም በሴራ ፖለቲከኞች ፕሮፖጋንዳ ግራ ቢጋባም ትምክህተኛ እና ነፍጠኛ መሆኑን ያውቃል። አጤ ምኒልክን፣ አጤ ኃይለስላሴን፣ አጤ ቴዎድሮስን፣ በላይ ዘለቀን….ወዘተ ሁሉ አማራ የሚያደርጋቸው እገሌ እንቶኔን ወለደ የሚል የዘር ቆጠራ አይደለም። ከፍ ያለ ትምክህተኝነታቸው እና ይህን ትምክህተኝነታቸውን የሚያስጠብቁበት ነፍጠኝነታቸው ነው። በመሆኑም ቅማንትነት እንደ ጎጃሜነት፣ እንደ አገውነት ..ወዘተ ያለ ንዑስ ማንነት ነው። ቅማንት ወሎየው እንደሚሆነው ሁሉ አማራ ነው።


አቶ ነጋ ጌጤ የተከተሉት የዘር ቆጠራ የቅማንት ንዑስ ማንነት ስነ-ልቦና የሚቆምበት መሰረት ከሚሆን በቀር የቅማንትን አማራነት የሚያስቀር አይደለም። ቅማንት አማራ ነው፤ አርጎባው አማራ እንደሆነው ሁሉ።

 

መውጫ፡-
የአማራ ብሄርተኝነት የቆመባቸው ምሰሶዎች ናቸው የተባሉት ትምክህተኝነት እና ነፍጠኝነት ምንድን ናቸው? በሚቀጥለው ሳምንት የምመለስበት ይሆናል።¾

ቢቢሲ የአማርኛ አገልግሎት ሰኞ ታህሳስ 2 ቀን 2010 (ዲሴምበር 11 /2017) «አዶ ሻኪሶ ወርቅ መርዝ የሆነባት ምድር» በሚል ርዕስ የሰራችሁትን ዘገባ ከድረገጻችሁ አግኝተን ተመልክተናል። ዘገባው በማወቅም ይሁን ባለማወቅ መሠረታዊ የሆነውን የጋዜጠኝነት መርህ ማለትም ሚዛናዊነት የሳተና ባለቤቱን በማግለል የአንድ ወገን አስተያየት ብቻ የተስተናገደበት መሆኑ በእጅጉ አሳዝኖናል። 

 

በዚህ ዘገባ ውስጥ ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ ተፈጥረዋል ተብለው በዘገባው ውስጥ ለተጠቀሱ ችግሮች ብቸኛ ተጠያቂ ተደርጎ ሲቀርብ ኩባንያው ግን እየተጠየቀበት ስላለው ጉዳይ መልስ እንዲሰጥ ዕድል ከመስጠት ይልቅ ሌሎች ወገኖች ባሉት ላይ ብቻ ተመስርቶ በይሆናል ወይንም በግምት የተዛባ ዘገባ ለማሰራጨት የተፈለገበት ምክንያት እስካሁንም ለእኛ እንቆቅልሽ ነው። እናም ሳንጠየቅና እየቀረበብን ላለው ክስ ምላሽ እንድንሰጥ ዕድሉ ሳይሰጠን የቀረበው ዘገባ ከጋዜጠኝነት ሙያ ሥነምግባር እና ከሞራልም አኳያ ቢቢሲን ያህል ትልቅ ተቋም የማይመጥን ስህተት በመሆኑ ሊታረም ይገባል እንላለን።

 

በዘገባው ውስጥ የሰፈሩ ተገቢ ያልሆኑ የስም ማጥፋት አስተያየቶች እንደሚከተለው ምላሻችንን እናቀርባለን፣

 

የሚድሮክ ለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ ወርቅና ነሐስ በሚያመርትበት ግዜ ወርቁን ለማጽዳት የሚጠቀምበት «ሳናይድ» የተባለ ኬሚካል በሰዎችና በአካባቢ ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ በዘገባው ተመልክቷል። በተጨባጭ ያለው እውነታ ግን ምንድነው የሚለውን ማየት ተገቢ ይሆናል። ህዳር 28 ቀን 2010 ዓ.ም (ዲሴምበር 7 ቀን 2017) በማዕድን ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ በየደረጃው የሚገኙ ጉዳዩ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው የክልልና ፌዴራል መንግሥታዊ አካላት፣ ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያን ጨምሮ የዘርፉ ባለሃብቶች በተገኙበት የተካሄደ ስብሰባ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ተነሰቷል። ምናልባትም ለዘገባችሁ የመጀመሪያ መነሻ ሃሳብ ይህ ስብሰባ ሊሆን እንደሚችል እንገምታለን። በዚህ ስብሰባ ላይ የኬሚካል ጉዳት ጉዳይ በተነሳበት ወቅት በመድረኩ የተገኙት የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰርና የሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ዋናሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ስለተጨባጭ ሁኔታው ማብራሪያ ሰጥተዋል። ሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ዓለም አቀፍ ደረጃን በሟላ ሁኔታ የአካባቢ ጥበቃ ተጽዕኖ ግምገማ (Environmental impact assessment) አስጠንቶ ወደሥራ የገባ ኩባንያና በሚኒስቴሩም ሆነ በሌሎች ሀገር በቀል ኩባንያዎች በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን ያስረዱ ሲሆን የተባለው የኬሚካል ችግር ፍጹም እንደሌለ፣ ያስረዱ ሲሆን ሆኖም ጥርጣሬዎችን ይበልጥ ለማጥራትና ሙሉ በሙሉ መተማመንን ለመፍጠር እንዲያግዝ የተጠቀሰውን ችግር ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ ጥናት ቢያካሂድ ለጥናቱ አስፈላጊውን ወጪ ኩባንያው እንደሚሸፍን ቃል ገብተዋል። በዚሁ መሠረት ሚኒስቴሩ ጉዳዩን ትኩረት በመስጠት ከኬሚካል ጋር ተያይዞ ተፈጠረ የተባለው ችግር እንዲጠና ተገቢውን መመሪያ በመድረኩ ላይ ሰጥቷል።

 

ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ የለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ በፕራቬታይዜሽን ሒደት ተላልፎለት ከመረከቡ በፊት «ሜሪኩሪ» የተባለ ኬሚካል ለማጣሪያ ጥቅም ላይ ይውል የነበረበት ሁኔታ እንደነበር የሚታወስ ነው። ሜሪኩሪ በሰዎችና በአካባቢ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ኩባንያችን አስቀድሞ በመገንዘብ ወደሥራ በሚገባበት ጊዜ በአሁኑ ሰዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለወርቅ ማጣሪያ የሚጠቀምበትን «ሳናይድ» የተባለ ኬሚካል መጠቀም ጀምሯል። ኩባንያችን ይህን ዓለም የተቀበለውን አሠራር የመረጠው በሕዝብና በአካባቢ ላይ ጉዳት እንዳይከተል በማሰብ ጭምር ነው። ኩባንያችን በተጨማሪም የአካባቢን ጉዳይ የሚከታተል ራሱን የቻለ ዲፓርትመንት በማቋቋም በየጊዜው ከአካባቢው ሕብረተሰብ ጋር በቅርበት በመገናኘትና በመወያየት እንዲሁም ለአካባቢ ጥበቃ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ዛፎች እንዲተከሉና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው በማድረግ ለአካባቢ ጥበቃ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ያለ ኩባንያ መሆኑም የሚታወቅ ነው።

 

ኩባንያችን ላይ የቀረበው ክስ በምርመራ ያልተረጋገጠ ስለመሆኑ፣

 

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን አዶ ሻኪሶ አካባቢ በማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ የተሠማራው ሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ብቻ አለመሆኑ ይታወቃል። ሌሎች የመንግሥትና የግል ባለሃብቶችም ከ60 ዓመታት በላይ በተመሳሳይ ሥራ ላይ መሆናቸው የሚታወቅ እውነት ነው። ከኬሚካል ጋር ተያይዞ ደረሰ የተባለው ጉዳት በእርግጥም የሚድሮክ ችግር ብቻ ስለመሆኑ የተጨበጠ ማስረጃ በሌለበት ሁኔታ በዘገባችሁ እርግጠኛ በመሆን ኩባንያችን ላይ ብቻ ያነጣጠረ አፍራሽና ጎጂ ዘገባ መቅረቡ ከሙያ ሥነምግባር ውጪ ነው። ችግሩ ተከስቷል እንኳን ቢባል በየትኛው ኩባንያ እንደተከሰተ ተጨማሪ ጥናትና ምርምር ማድረግን ይጠይቃል። ባለቤቱን ቀርቦ ማነጋገርና ተገቢውን መረጃ መሰብሰብ ይጠይቃል። እንዲሁ በስሜት የሚደረግ ዘገባ በርካታ ሠራተኞች በማቀፍ ለአገር ኢኮኖሚ አዎንታዊ ሚና የሚጫወተውን እንደእኛ ያለ ኩባንያ የሚጎዳ ብቻ ሳይሆን በሕግም ጭምር የሚያስጠይቅ የስም ማጥፋት ወንጀል ነው።

 

የደረሰ ጉዳት የሌለ ስለመሆኑ፣


ኩባንያችን አካባቢ በጠበቀና ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የሚሠራ በመሆኑ በአካባቢ ላይም ሆነ በሰዎች ላይ ከኬሚካል ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ችግር የለም። ይህን የምንለው በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን ማህበራዊ ችግሮቹን ጭምር እየተካፈልን የምንሰራ በመሆናችን እንደዚህ ያለ ትልቅ ችግር ቀርቶ አነስተኛ ችግሮችም ቢኖሩ የምናውቅበትና፤ ችግር ተከስቶም ከሆነ በወቅቱ የምናርምበት ዕድል ሰፊ በመሆኑ ነው።


ከላይ በተጠቀሰው ስብሰባ በማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የአካባቢና የማህበረሰብ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ባደረግነው ክትትልና ቁጥጥር ሒደት በኬሚካል የደረሰ ጉዳት አላየንም፣ ከማህበረሰብም ሆነ ከመንግሥት አካል የደረሰን ቅሬታ የለም በሚል መግለጫም ሰጥተዋል።

 

የህብረተሰቡን ማህበራዊ ችግሮች መካፈልን በተመለከተ፣


ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን የአካባቢው ማህበረሰብ ከልማቱ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህ መሠረት ኩባንያው ባለፉት ዓመታት በአብዛኛው በራሱ ተነሳሽነት የአካባቢውን ማህበረሰብ የሚጠቅሙ እንደትምህርት ቤቶች፣ የጤና ኬላዎች፣ የመንገድ ግንባታና የመሳሰሉትን የልማት ተግባራት አከናውኗል። የአካባቢው ወጣቶችም ለሥራ ዕድል ቅድሚያ ከመስጠት ጀምሮ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የነጻ ትምህርት ዕድል እስከመስጠት የዘለቀ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህ እውነታ የሚታይና ሌላ ማንም ሳይሆን እዚያው በልማቱ ተጠቃሚ የሆነው ሰፊው ሕዝብ የሚመሰክረው ነው። በተጨማሪም ይህ እውነታ በክልሉም ሆነ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚታወቅ መሆኑን፣ ተጨማሪ ዝርዝር ግልጽ መረጃ ያለው መጽሔትም በየጊዜው ስናወጣ መቆየታችን ማስታወስ እንወዳለን።


በተጨማሪም የኩባንያው የጥበቃ ሠራተኞች በአካባቢው ነዋሪ ላይ ልዩ ልዩ ችግሮችን ያደርሳሉ በሚል በዘገባው የተካተተ ቅሬታ አለ። በመሠረቱ ኩባንያው ውስጥ በርካታ ሠራተኞች ከአካባቢው ተቀጥረው ተጠቃሚ ሆነዋል። ኩባንያችን በዓመት ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ለደመወዝ ብቻ ወጪ በማድረግ የአካባቢው ህብረተሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በተግባር ማሳየት የቻለ ኩባንያ ነው። በዚህ ሒደት አልፎ አልፎ የሥራ ዕድል ያልደረሳቸው ግለሰቦች ቅሬታ ሊያቀርቡ ቢችሉም ይህ ቅሬታ ሰፊውን ህብረተሰብ የሚወክል ተደርጎ መቅረቡ የተሳሳተ ጥቅል ድምዳሜ ሆኖ አግኝተነዋል። የኩባንያው የጸጥታ አስከባሪ ሠራተኞችም በተመሳሳይ ሁኔታ ከአካባቢው ህብረተሰብ የወጡና ህብረተሰቡ የሚያውቃቸው ግለሰቦች ናቸው። እነዚህ ሠራተኞቻችን በተለየ ሁኔታ የአካባቢው ህብረተሰብ ላይ ችግር ለመፍጠር ይንቀሳቀሳሉ የሚለው አስተያየት በምንም መመዘኛ አሳማኝ አይደለም። ምናልባት በተለየ ሁኔታ ችግር ደርሶብኛል የሚል ግለሰብ ካለ ቅሬታውን አቅርቦ ልናየው የምንችለው ከመሆኑ በስተቀር ሕብረተሰቡ በጅምላ ቅሬታ የሚያቀርብበት ሁኔታ አለመኖሩን ማረጋገጥ እንወዳለን።

 

የገቢ ግብር ግዴታን ከመወጣት አንጻር፣


ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን በሮያሊቲ፣ በተለያዩ የግብር ክፍያዎች ከአጠቃላይ ገቢው እስከ 50 በመቶ ወጪ በማድረግ በየዓመቱ ለፌዴራልና ለክልል መንግሥታት ገቢ ያደርጋል። በዚህም ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ያለና ሕግና ሥርዓትን አክብሮ የሚሠራ ኩባንያ መሆኑም ይታወቃል። በሥራ ፈጣሪነትም በፕራቬታይዜሽን የተረከበውን 600 ሠራተኞች ቁጥር ወደ 1200 በማድረስና በዓመት 140 ሚሊየን ብር ለሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማጥቅሞች የሚከፍል ተሸላሚ ኩባንያ ነው።

 

በመጨረሻም፡- ቢቢሲን ጨምሮ ማናቸውም መገናኛ ብዙሃን ኩባንያችንን በሚመለከት ለሚያቀርቡልን የመረጃ ጥያቄ በራችን መቼም ቢሆን ክፍት መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እያረጋገጥን በዘገባችሁ የተሰራው ስህተት ከኩባንያው አልፎ አገርንም የልማት ሒደት የሚደናቅፍ ሥራ ስለሆነ እንዲታረም እንጠይቃለን።


- ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ እና ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሕዝብ ግንኙነት ክፍሎች 

 

የኢፌዲሪ ፓርላማ ጥቅምት 2 ቀን 2010 ዓ.ም ተቀብሎ ከተመለከታቸው አጀንዳዎች አንዱ የፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ ይገኝበታል። አዋጁ በማሻሻያነት ካካተታቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል ለሴት የመንግስት ሠራተኞች የሚሰጠው የድህረ ወሊድ ፈቃድ ከ60 ወደ 90 ቀናት ከፍ እንዲል ማድረጉ፣ የጽንስ መቋረጥ ላጋጠማት ሴት ሠራተኛ እስከ ሦስት ወር የሚደርስ ዕረፍት መፍቀዱ በዋናነት ይጠቀሳል።

ይህ ረቂቅ አዋጅ የተመራላቸው የምክርቤቱ የሰው ሀብት ልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ሚ ኮምቴ እና የሕግና ፍትሕ አስተዳደር ሚ ኮምቴ ጉዳዩ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተከታታይ ውይይቶችን ካደረጉ በላ ከጥቂት ማሻሻያዎች ጋር አዋጁ እንዲጸድቅ የውሳኔ ሃሳብ በትላንትናው ዕለት አቅርበዋል፡፡ ም/ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተወያይቶ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

በዚህ አዋጅ ድንጋጌ መሠረት የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ ክርክር የሚመለከቱ የአስተዳደር ፍርድቤቶች የሚቋቋሙ ሰሆን የፍርድቤቶቹ ውሳኔ የህግ ስህተት አለበት የሚል ይግባኝ ካልቀረበበት በስተቀር የመጨረሻ እንደሚሆን ተደንግል፡፡ የአስተዳደር ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ አስፈጻሚ አካላት በደረሳቸው በአስር ቀናት እንዲፈጽሙ አስገዳጅ አንቀጽ በማሻሻያው ውስጥ ተካል፡፡

የአስተዳደር ፍ/ቤቱ በመንግሥት ሠራተኞች የሚቀርቡለትን ይግባኞች ማለትም ከሕግ ውጪ ከሥራ መታገድ ወይንም አገልግሎት መረጥ፣ ከባድ የዲስፒሊን ቅጣት መጣልን በመቃወም ቅሬታ ሲቀርብ፣ ከሕግ ውጪ የደመወዝና ጥቅማጥቅም ሲረጥ፣ በሥራ ምክንያት በደረሰ ጉዳት የመብት መደል፣ ከሥራ ለመልቀቅና የአገልግሎት ማስረጃ ለማግኘት ከቀረበ ጥያቄ ጋር በተያያዙ የሚነሱ ቅሬታዎችን ተቀብሎ ይመለከታል፡፡

በአዋጁ ላይ ከሚቀርቡ ቅሬታዎች በጥቂቱ

አንድ የመንግሥት ሠራተኛ የሥራ ውል በሚያቋርጥበት ጊዜ ሠራተኛው ለሥራው እጅግ አስፈላጊ ከሆነ አሰሪው ወደፊት ከሚቀጠርበት መ/ቤት ጋር በመስማማት ሠራተኛው ካመለከተበት ቀን ጀምሮ ከሶስት ወር ለማይበልጥ ጊዜ መልቀቂያውን ሊያራዝመው እንደሚችል የተቀመጠው ድንጋጌ አንዳንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የመንግስት ሠራተኞች «የመንግሥትን ጥቅም ብቻ ለማስከበር ያለመ» ሲሉት ተቃውመውታል፡፡ አስተያየት ሰጪው እንዳሉት አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ሥራውን ሲለቅ ቀጥሎ የሚሄድበትን መ/ቤት ያለመግለጽ መብት አለው፡፡ ስለሆነም የሚለቀው መ/ቤት ተመካክሮ የመልቀቂያ ጊዜውን ሊያራዝምለት የሚችልበት ዕድል አይኖረውም፡፡ ወይንም ሠራተኛው የሚለቀው በግል ድርጅት ለመቀጠር ወይንም የግል ሥራ ለመጀመር ወይንም ወደሌላ አገር ለመሄድ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ሠራተኛ በቀላሉ መተካት አልችልም በሚል ሰበብ መልቀቂያውን ለሶስት ወራት መከልከል ኢ ሕገመንግሥታዊ ነው ብለውታል፡፡ በተጨማሪ ይህ አንቀጽ ሕግና ሥርዓትን አክበረው ለማይሰሩ ቢሮክራት ሥራ መሪዎችና ኪራይ ሰብሳቢ አመራሮች መጠቀሚያ ትልቅ ክፍተት የተወ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሌላው በአዋጁ የተካተተውና ለአስፈጻሚው አካል ያልተገባ መብት የሚሰጠው በችሎታ ማነስ ከሥራ ማሰናበትን የሚመለከተው አንቀጽ ነው፡፡ አንድ የሙከራ ጊዜው ያጠናቀቀ የመንግሥት ሠራተኛ ተገቢውን የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተሰጥቶት በሥራ አፈጻጸም የችሎታ ማነስ ከታየበት አገልገሎቱ እንደሚቋረጥ መደንገጉ ነው፡፡ በተጨማሪም ለተከታታይ ሶስት ጊዜ የሥራ አፈጻጸሙ ከሚጠበቀው በታች የሆነ ሠራተኛ እንደሚሰናበት ይደነግጋል፡፡ እነዚህ አንቀጾች ሠራተኞች በተለይ ሙስናና ብልሹ አሠራርን በመዋጋት ወይንም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ በየጊዜው ሃሳቦች በማቅረባቸው ምክንያት ብቻ በአንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢ አመራር በቀላሉ የጥቃት ኢላማ ልንሆን እንችላለን የሚል ሥጋትን አሳድሯል፡፡

 

 

አዋጁ ለእናቶች ያስገኘው ልዩ ጥቅም

ለሴት የመንግስት ሠራተኞች የሚሰጠው የድህረ ወሊድ ፈቃድ ከ60 ቀን ወደ 90 ቀናት ከፍ እንዲል ተደርጓል። ይሄም የሆነበት ምክንያት ህፃኑን ለመንከባከብ በቂ የእረፍት ጊዜ ሊያገኙ እንደሚገባ በህክምና ባለሙያዎች አስተያየት የተሰጠ በመሆኑና የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮም እንደሚያመለክተው ከወሊድ በኋላ ሦስት ወር ፈቃድ የሚሰጡበት ሁኔታ በመኖሩ እንዲሻሻል ተደርጓል።

በዚሁ መሠረት ነፍሰ ጡር የሆነች የመንግሥት ሠራተኛ ከእርግዝናው ጋር ተያይዞ ምርመራ ለማድረግ ሐኪም በሚያዘው መሠረት ደመወዝ የሚከፈልበት ፈቃድ እንደምታገኝ፣ ከመውለዷ በፊት ዕረፍት እንድታደርግ ሐኪም ካዘዘ ደመወዝ የሚከፈልበት ዕረፍት እንደሚሰጣት በረቂቅ አዋጁ ተካትቷል። ይህ ፈቃድም እንደ ሕመም ፈቃድ አይቆጠርም ብሏል።

በተጨማሪም ነፍሰጡር የሆነች የመንግሥት ሠራተኛ መውለጃዋ ሲደርስ እወልዳለሁ ብላ ከገመተችበት ቀን በፊት 30 ተከታታይ ቀናት የቅድመ ወሊድ ፈቃድ እንዲሁም ስትወልድ ከወለደችበት ቀን ጀምሮ 90 ተከታታይ ቀናት በአጠቃላይ 120 ተከታታይ ቀናት ደመወዝ የሚከፈልበት የወሊድ ፈቃድ እንደሚሰጣት ተደንግጓል። ሠራተኛዋ የተሰጣት የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ከማለቁ በፊት ከወለደች ያልተጠቀመችበት ቀሪ የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ከወለደች በኋላ እንድትጠቀምበት ይደረጋል።

ሠራተኛዋ የወሰደችው ቅድመ ወሊድ ፈቃድ ሲያልቅ ያልወለደች እንደሆነ እስከምትወልድበት ቀን ድረስ ባሉት የሥራ ቀናት የምትቆይበት ዕረፍት በበጀት ዓመቱ ካላት የዓመት ዕረፍት ፈቃድ ወይም በበጀት ዓመቱ የዓመት ፈቃድ የሌላት እንደሆነ ከሚቀጥለው የበጀት ዓመት የዕረፍት ፈቃዷ ይተካል።

ሠራተኛዋ የተወሰነውን የወሊድ ፈቃድ ከጨረሰች በኋላ ብትታመምና ተጨማሪ ፈቃድ የሚያስፈልጋት መሆኑ በሐኪም ከተረጋገጠ የህመም ፈቃድ መውሰድ እንደምትችል በረቂቅ አዋጁ ላይ ተመልክቷል።

በሥራ ላይ ያለው አዋጅ የጽንስ መቋረጥ ያጋጠማቸው ሴት ሠራተኞች ከወሊድ ፈቃድ ጋር በተያያዘ በምን መልኩ እንደሚስተናገዱ ያላመለከተ በመሆኑና ህይወት ያለው ህጻን በወለደችና ጽንሱ በተጨናገፈባት ሴት መካከል ልዩነት የፈጠረ በመሆኑ፣ በተለይም ጽንስ የተቋረጠባት ሠራተኛ የጤናና የስነ ልቦና ችግር የሚያጋጥማት በመሆኑ ከዚህ ችግር አገግማ ወደ ስራዋ እንድትመለስ ባለሙያዎች በቂ ፈቃድ ሊሰጣት እንደሚገባ አስተያየት የሰጡ ከመሆኑም በላይ መንግስት በፖሊሲዎቹና በስትራቴጂዎቹ በሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ላይ ልዩ ትኩረት ከመስጠቱ አንጻር ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ድንጋጌ ማካተት በማስፈለጉ በረቂቅ አዋጁ እንዲካተት ተደርጓል።

ረቂቅ አዋጁ እንደሚለው ማንኛውም ስድስት ወር የሞላት ነፍሰ ጡር የሆነች የመንግሥት ሠራተኛ የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ከመውሰዷ በፊት ጽንሱ የተቋረጠባት ከሆነ ይህንን የሚያረጋግጥ የህክምና ማስረጃ ስታቀርብ የ60 ቀናት የድህረ ወሊድ ፈቃድ ይሰጣታል።

የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ከወሰደች በኋላ የጽንስ መቋረጥ ካጋጠማት የወሰደችው ቅድመ ወሊድ ፈቃዷ ተቋርጦ የ90 ቀናት የድህረ ወሊድ ፈቃድ ይሰጣታል።

ከሶስት እስከ ስድስት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ የጽንስ መቋረጥ ያጋጠማት የመንግስት ሠራተኛ ደመወዝ የሚከፈልበት የ30 ቀናት ፈቃድ ይሰጣታል።

በተጨማሪም የወሊድ ፈቃድ የሚሰጥበት መሠረታዊ ምክንያት ነፍሰጡር የሆኑ ሴቶች ከእርግዝና ጋር በተያያዘ የሚፈጠርባቸውን የጤና ችግርና በዚሁ ምክንያት የነፍሰጡሯንም ሆነ የጽንሱን ወይም የተወለደውን ህጻን ደህንነት ከማረጋገጥ ጋር የተያያዘ ቢሆንም የጽንስ መቋረጥ የሚያጋጥማቸው ሴቶች የበለጠ የጤናና የስነ ልቦና ችግር ስለሚያጋጥማቸው ይህንኑ በህመም ፈቃድ እንዲጠቀሙ መደረጉ አግባብ ባለመሆኑ፣ በተለይም የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ከወሰዱ በኋላ የፅንስ መቋረጥ የሚያጋጥማቸው ሴቶች የመውለጃ ወራቸው ከገባ በኋላ በመሆኑ የፅንስ መቋረጥ ያጋጠመበት ጊዜ መሠረት በማድረግ የቅድመ ወሊድ ወይም የድህረ ወሊድ ፈቃድ የምትጠቀምበት አሠራር እንዲካተት ተደርጓል።

ባል የትዳር አጋሩ ስትወልድ የሚፈቀደው የ5 ቀን ፈቃድ በቂ አለመሆኑን በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ ከመሆኑም በላይ በተግባር እንደታየው ሠራተኛው በዚህ ወቅት ቤተሰቡንና ባለቤቱን የመንከባከብ ኃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ ስለሚረከብ፣ በተለይም ባለቤቱ ሀኪም ቤት ውስጥ ለመንከባከብ ከዓመት ፈቃዱ እየወሰደ እንደሚያስታምም በተግባር የታየ በመሆኑ ወንዶች የአጋርነታቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል 10 ቀናት እንዲሰጠው በሚል እንዲሻሻል ተደርጓል።¾

ላለፉት ዘጠኝ ወራት ኢህአዴግን ጨምሮ 17 ፓርቲዎች በአስራ ሁለት አጀንዳዎች ላይ ለመደራደር ተስማምተው ድርድር ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ፓርቲዎቹ በእስካሁኑ ቆይታቸው በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ላይ ተደራድረዋል። በአሁን ሰዓት በምርጫ ሕግ አዋጅ ላይ እየተደራደሩ ይገኛሉ። በቀጣይ በጸረሽብር ሕጉ፣ በመገናኛ ብዙሃን የመረጃ ነጻነት ሕግ፣ በበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅ፣ በታክስ አዋጅ፣ በመሬት ሊዝ አዋጅና በመሳሰሉት ድርድር ያካሂዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የፓርቲዎቹ ቀጣይ የድርድር አጀንዳ የጸረ ሽብር ሕጉን የሚመለከት መሆኑም ታውቋል። በተለይ የጸረ ሽብር አዋጁ 652/2001 ኢህአዴግም ለመደራደር ፍላጎት ያሳየው ያለምንም ምክንያት አይደለም። ሕጉ በረቂቅ ደረጃ ጀምሮ እስካሁን ከፍተኛ ተቃውሞና ትችት የሚቀርብበት መሆኑም ይታወቃል። የፓርቲዎቹ ድርድር ከሞላ ጎደል ለቅሬታዎች መልስ በሚያስገን መልኩ ሕጉን ሊያሻሽል ይችላል ተብሎ ይገመታል።

የጸረ ሽብር ሕጉ ከሚነሳበት በርካታ ቅሬታዎች አንዱና ግንባር ቀደሙ ከሕገመንግሥቱ ጋር የሚጋጩ አንቀጾችን ይዟል የሚለው ይገኝበታል። አዋጁ ሽብር ምንድነው? ሽብርተኛስ ማንነው የሚለውን በግልጽ አይፈታውም። አዋጁ “ሽብርተኛ ድርጅት” በሚል ያስቀመጠው ፍቺ ላይ ሁለት እና ከዚያ በላይ አባላት ያሉት ቡድን ወይንም ማህበር ሆኖ የሽብር ድርጊትን የመፈጸም ዓላማ የያዘ ወይም የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም ያቀደ፣ የተዘጋጀ፣ የፈጸመ፣ ያስፈጸመ፣ እንዲፈጸም በማናቸውም ሁኔታ የረዳ ወይንም በፓርላማው በሽብርተኝት የተሰየመ ድርጅት ሽብርተኛ እንደሚባል አስቀምጧል። “ሽብር” የሚባለው ድርጊት ግን ሁለት ሰዎች ተገናኝተው ምን ሲደርጉ ነው የሚለው ግልጽ አይደለም። እንደሚታወቀው ሁለት ሰዎች ተገናኝተው መንግሥትን ሊያሙት ይችላሉ። “መንግሥት አልበጀንም ይውረድ” ብለው መፈክር ሊያሰሙ፣ በየአደባባይ እየዞሩ ሊጮሁ ይችላሉ። ወይንም በብስጭት መንፈስ ተነሳስተው ድንጋይ ሊወረውሩ ይችላሉ። ግን በሽብር ደረጃ ጥፋት ሊሆን የሚችለው ምን ሲፈጸም ነው የሚለው አይታወቅም። እናም ሕግ አስከባሪው አካል ጠርጥሮ ከያዘ በሀላ በሽብርተኝነት ክስ ቢያቀርብ ከልካይ የማይኖረው ከጅምሩ ሕጉ ግልጽ ባለመሆኑ ነው።

ሌላው በሕጉ ውስጥ እንደሽብርተኝነት ድርጊት በትርጉም መልክ በክፍል ሁለት በአንቀጽ 3 የተቀመጠው እንዲህ ይላል። ማንኛውም ሰው ወይም ቡድን የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም አይዲዎሎጂ ዓላማን ለማራማድ በማሰብ በመንግሥት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር፣ ህብረሰቡን ወይም የህብረተሰቡን ክፍል ለማስፈራራት ወይም የሀገሪቱን መሠረታዊ ፖለቲካዊ፣ ህገመንግሥታዊ ወይም ማህበራዊ ተቋማትን ለማናጋት  ወይም ለማፍረስ በሰውና በንብረት፣ በተፈጥሮ ሀብት ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ በሽብር ወንጀል እንደሚቀጣ ተደንግጓል።

በአንቀጽ 6 ላይ ደግሞ ሽብርተኝነትን ስለማበረታታ በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር የሽብርተኝነት ድርጊት እንዲፈጸም ወይም ለመፈጸም እንዲዘጋጁ የሚያበረታታ ጹሑፍ ያተመ፣ ያሳተመ በሽብር ወንጀል እንደሚጠየቅ ይደነግጋል።

ሌላው በአንቀጽ 14 መረጃ መሰብሰብ በሚል ንዑስ ርዕስ ስር ብሔራዊ የመረጃና የደህንነት ተቋም ያለፍርድ ቤት ፈቃድ በሽብርተኝነት የተጠረጠረን ሰው የግል ግንኙነቶች ማለትም የስልክ፣ የፋክስ፣ የራዲዮ፣ የኢንተርኔት፣ የፖስታና የመሳሰሉትን ለመጥለፍ ወይንም ለመከታተል ይፈቅድለታል።

እንዲሁም በአንቀጽ 17 የሽብርተኝነት ድርጊት አስቀድሞ ለመከላከል ሲባል ከፍርድ ቤት በጹሑፍ ወይንም በቃል ፈቃድ ጠይቆ በድብቅ ብርበራ ማካሄድ እንደሚችል ይደነግጋል።

ሌላው አከራካሪና ቅሬታ የሚቀርብበት አንቀጽ 23 ነው። በዚህ አንቀጽ ውስጥ ተቀባይነት የሚኖራቸው ማስረጃዎችን በተመለከተ የሰሚ ሰሚ ወይንም በተዘዋዋሪ የተገኙ ማስረጃዎች ለፍርድ ቤት መቅረብ የሚችሉ መሆናቸው ይደነግጋል።

እነዚህ ድንጋጌዎች በኢትዮጵያ ሕገመንግሥት የተደነገገውን የሃይማኖት፣ የእምነትና አመለካከትን በነጻነት የማራመድ መብት፣ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት፣ የመንግሥት አሠራር ተጠያቂነት፣ የመሰብሰብ፣ ሠላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት፣ የግል ነጻነት መብት በቀጥታና በተዘዋዋሪ ይገድባል፣ ይጻረራል በሚል ቅሬታ ይቀርብበታል። በዚህ አንቀጽ መሠረት በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች ሕዝብ የሚያሳየው ሀይል የቀላቀለበት የፖለቲካ ተቃውሞ የሽብር ወንጀል ነው ማለት ነው። መገናኛ ብዙሃን አንድን ጹሑፍ ከማተማቸው በፊት ጹሑፉ ከሽብር ጉዳይ ጋር ንክኪ ይኑረው ወይንም አይኑረው በምን ማረጋገጥ እንደሚችሉ በአዋጁ ላይ የተቀመጠ ነገር የለም። የግል መብትን የሚያጣብቡ ወይንም የሚጥሱ ብርበራዎችና ጠለፋዎች እንዲሁ ከሕገመንግሥቱ አንጻር ሊታዩ የሚገባቸው ናቸው። የማስረጃ አቀራረብን በተመለከተ በተለይ የሰሚ ሰሚ ማስረጃ ማለትም «እኔ ወንጀሉን ሲፈጽም አላየሁም፣ የማውቀው ነገርም የለኝም። ነገርግን እንዲህ ፈጽሟል ብሎ እከሌ ነግሮኛል» ዓይነት ደካማ አሉባልታ መሰል ወሬዎች (ማስረጃዎች) መሠረት አድርጎ የፍትህ ሒደትን መምራት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ሊያደርስ የሚችልበት ዕድል ስለሚኖረው አንቀጹ መታየት የሚኖርበት ነው።

በሽብርተኝነት የሚገኝ ንብረት መውረስ ድንጋጌም በተመለከተ አከራካሪ ጉዳዮች አሉበት። አንደኛ ወንጀለኛው ከሽብር ገቢ ጋር በተያያዘ የገዛውን ንብረት በላቡ ከገዛው ጋር የመለየቱ ጉዳይ አስቸጋሪ መሆኑ፣በትዳር ጓደኛ እና ልጆች (ቤተሰቦች) የይገባኛል ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑ በተግባር የታየ ነውና ይህም አንቀጽ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ነው።

በአጠቃላይ የጸረ ሽብር ሕጉ በሥራ ላይ ከዋለ በሃላ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና አባላትን እንደሁም ጋዜጠኞችን ለይቶ ለማጥቂያነት ጥቅም ላይ ውሏል የሚለውን ቅሬታ ገዥው ፓርቲ አሳማኝ ምላሽ መስጠትም ይጠበቅበታል።

በፓርቲዎቹ ድርድር አወዛጋቢው የጸረ ሽብር ሕግ ሊሻሻል ይችላል የሚለው የብዙዎች ተስፋ ሆኗል።

 

ከፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር ፮፻፶፪/፪ሺ፩

አንዳንድ አንቀጾች እነሆ

ክፍል ሁለት

ስለሽብርተኝነት እና ተያያዥ ወንጀሎች

፫. የሽብርተኝነት ድርጊቶች

ማንኛውም ሰው ወይም ቡድን የፖለቲካ፣ የሃይማኖታዊ ወይም የአይዲዮሎጂ ዓላማን ለማራመድ በማሰብ በመንግሥት ላይ ተፅኖ ለማሳደር፣ ህብረተሰቡን ወይም የህብረተቡን ክፍል ለማስፈራራት ወይም የሀገሪቱን መሠረታዊ ፖለቲካዊ፣ ህገመንግሥታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ማህበራዊ ተቋማትን ለማናጋት ወይም ለማፍረስ፡-

፩. ሰውን የገደለ ወይም በአካሉ ላየ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ፤

፪. የህብረተሰቡን ወይም የህብረተሰቡን ክፍል ደህንነት ወይም ጤና ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጠ እንደሆነ፡-

፫. እገታ ወይም ጠለፋ የፈፀመ እንደሆነ፤

፬. በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ፤

፭. በተፈጥሮ ሀብት፣ በአካባቢ፣ በታሪካዊ ወይም የባህል ቅርስ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ፤

፮. ማናቸውንም የህዝብ አገልግሎት ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጠ፣ የያዘ፣ በቁጥጥር ስር ያደረገ፣ ያቋረጠ ወይም ያበላሸ እንደሆነ፤ ወይም

፯. በዚህ አንቀጽ ከንዑስ አንቀጽ (፩) እስከ (፮) ከተመለከቱት ድርጊቶች መካከል ማናቸውንም ለመፈፀም የዛተ እንደሆነ፤

ከ፲፭ ዓመት እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ ፅኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል።

 

 

፬. የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈፀም ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማሴር፣ ማነሳሳትና ሙከራ

ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ በአንቀጽ ፫ ከንዑስ አንቀጽ (፩) እስከ (፮) የተመለከተውን ማናቸውንም የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈፀም ያቀደ፣ የተዘጋጀ፣ ያሴረ፣ ያነሳሳ ወይም የሞከረ እንደሆነ በዚሁ አንቀጽ በተቀመጠው መሠረት ይቀጣል።

 

፭/ ለሽብርተኝነት ድጋፍ መስጠት

፩. ማንኛውም ሰው የሽብርተኝነት ድርጊት አፈፃፀምን ወይም የሽብርተኛ ድርጅትን የሚረዳ መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው፡-

ሀ. ሀሰተኛ ሰነድ ያዘጋጀ፣ ያቀረበ ወይም የሰጠ እንደሆነ፤

ለ. የሙያ ፣ የልምድ የሞራል ምክር ወይም ድጋፍ የሰጠ እንደሆነ፤

ሐ. ማናቸውንም ዓይነት ንብረት በማናቸውም ሁኔታ ያቀረበ፣ ያሰባሰበ ወይም እንዲቀርብ ያደረገ እንደሆነ፤

መ. የገንዘብ ወይም የፋይናንስ ወይም ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው አገልግሎቶችን ያቀረበ ወይም የሰጠ እንደሆነ፤

ሠ. ማናቸውንም ፈንጂ፣ ዳይናሚት፣ ሊቀጣጠል የሚችል  ነገር፣ የጦር መሳሪያ ወይም ሌላ ገዳይነት ያለው መሳሪያ ወይም መርዛማ ነገር ያቀረበ ወይም የሰጠ እንደሆነ፤ ወይም

ረ. ማናቸውም አይነት ሥልጠና ወይም ትምህርት ወይም መመሪያ የሰጠ እንደሆነ፤

ከ፲ እስከ ፲፭ ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል።

፪. ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ የተመለከተ የሽብርተኝነት ድርጊት የፈፀመ መሆኑን እያወቀ ለማንኛውም ሰው ከለላ የሰጠ ወይም እንዲያመልጥ የረዳ ወይም የደበቀ እንደሆነ ከ፲ ዓመት እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል።

 

፮. ሽብርተኝነት ስለማበረታታት

ማንኛውም ሰው መልዕክቱ እንዲታተምላቸው የተደረገው የህብረተሰቡ አባላት በከፊል ወይም በሙሉ በዚህ አዋጅ በአንቀጽ ፫ የተመለከተ ማናቸውንም የሽብርተኝነት ድርጊት እንዲፈፅሙ ወይም ለመፈፀም እንዲዘጋጁ ወይም እንዲነሳሱ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያበረታታቸው ወይም በማናቸውም ሌላ ሁኔታ የሚገፋፋቸው እንደሆነ አድርገው ይረዱታል ተብሎ ሊገመት የሚችል  መልዕክት ሆነ ብሎ ወይም በግዴለሽነት ያተመ ወይም ያሳተመ እንደሆነ ከ፲ እስከ ፳ ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል።

 

፯. በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ ስለመሳተፍ

፩. ማንኛውም ሰው ለሽብርተኛ ድርጅት ወይም የሽብርተኝነት ድርጊቶችን ለመፈፀም ሰው የመለመለ ወይም አባል የሆነ ወይም ስልጠና የወሰደ ወይም በድርጅቱ በማናቸውም መልክ የተሳተፈ እንደሆነ እንደየተሳትፎ ደረጃው ከ፭ እስከ ፲ ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል።

 

፷. ለሽብርተኝነት ድርጊት መፈፀሚያነት እንዲውል ንብረት መያዝ ወይም መጠቀም

ማንኛውም ሰው የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈፀም ወይም እንዲፈፀም ለማመቻቸት እንደሚውል እያወቀ ወይም እንዲውል በማሰብ ማናቸውንም ንብረት የያዘ ወይም የተጠቀመ እንደሆነ፣ የንብረቱ መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከ፭ እስከ ፳ ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል።

 

፱. በሽብርተኝነት ድርጊት የተገኘን ንብረት ስለመያዝና መገልገል

ማንኛውም ሰው ከሽብርተኝነት ድርጊት የተገኘ ንብረት መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው አንድን ንብረት በባለቤትነት የያዘ ወይም በይዞታው ስር ያደረገ ወይም የተጠቀመ ወይም የለወጠ ወይም የደበቀ ወይም ያመሳሰለ እንደሆነ፣ የንብረቱ መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከ፭ እስከ ፲፭ ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል።

 

፲. ምስክር ማባበል ወይም ማስፈራራትና ማስረጃ ማጥፋት

ማንኛውም ሰው፤

፩. በሽብርተኝነት ድርጊት ላይ ምስክር የሆነን ወይም ለመሆን የሚችል ሰውን እንዳይመሰክር የደለለ ወይም ያስፈራራ ወይም በምስክሩ ወይም ከምስክሩ ጋር የቅርብ ግንኙነት ባለው ሰው ላይ የሃይል ድርጊት የፈፀመ እንደሆነ፣ ወይም

፪. ማስረጃ ያጠፋ ወይም የደበቀ እንደሆነ፤

ከ፭ እስከ ፳ ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።

 

፲፩. በሀሰት የሽብርተኝነት ድርጊት ስለማስፈራራት

ማንኛውም ሰው ሀሰተኛ መሆኑን እያወቀ ወይም እያመነ የሽብርተኝነት ድርጊት እንደተፈፀመ ወይም እየፈፀመ እንደሆነ ወይም እንደሚፈፀም በማናቸውም መንገድ ለሌላ ሰው ሆን ብሎ የገለፀ እንደሆነ ከ፫ እስከ ፲ ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል።

 

፲፪. የሽብርተኝነት ድርጊቶችን አለማስታወቅ

ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ የተመለከተ የሽብርተኝነት ድርጊት ሳይፈፀም ለመከላከል የሚረዳ መረጃ እያለው ወይም የሽብርተኝነት ድርጊትን የፈፀመን ወይም ሊፈፅም የተዘጋጀን ሰው ለመያዝ ወይም ለመክሰስ ወይም ለማስቀጣት የሚያስችል መረጃ ወይም ማስረጃ እያለው ያለበቂ ምክንያት መረጃውን ወይም ማስረጃውን ለፖሊስ ወዲያውኑ ያልገለፀ ወይም ሀሰተኛ መረጃ የሰጠ እንደሆነ ከ፫ እስከ ፲ ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።

….....

፲፬. መረጃ ስለማሰባሰብ

፩. የሽብርተኝነት ድርጊትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍርት ቤት ፈቃድ በመውሰድ፡-

ሀ. በሽብርተኝነት ወንጀል የተጠረጠረን ሰው የስልክ፣ የፋክስ፣ የሬድዮ፣ የኢንተርነቴት፣ የኤሌክትሮኒክስ፣ የፖስታና የመሳሰሉ ግንኙነቶችን ለመጥለፍ ወይም ለመከታተል፤

ለ. ጠለፋውን ለማስፈፀም ወደ ማናቸውም ቤት ውስጥ በሚስጥር ለመግባት፤ ወይም

ሐ. ይህንኑ ለመፈፀም የሚያስችሉ መሳሪያዎችን ለማስቀመጥ ወይም ለማንሳት፤ ይችላል።

፪/ በጠለፋ የሚገኝ መረጃ በምስጢር መጠበቅ አለበት።

፫/ ማናቸውም የመገናኛ አገልግሎት አቅራቢ በብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ጠለፋውን ለማካሄድ ሲጠየቅ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ አለበት።

፬/ የሽብርተኝነት ድርጊትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ወይም ፖሊስ ክትትል በማድረግ መረጃዎችን ሊያሰባስብ ይችላል።

 

፲፭. ተከራይን ስለሚለከቱ መረጃዎች

፩/ ማንኛውም ቤት፣ ቦታ፣ ክፍል ወይም ተሽከርካሪ ወይም ተመሳሳይ መገልገያ አከራይ የሆነ ሰው የተከራዩን ማንነት በዝርዝርና በፅሁፍ የመያዝ እና በአቅራቢያው ላለ ፖሊስ ጣቢያ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የማሳወቅ ግዴታ አለበት።

፪/ ማንኛውም ሰው በቤቱ ውስጥ የውጭ ሀገር ዜጋን ሲያኖር በአቀራቢያው ላለ ፖሊስ ጣቢያ ስለሚያኖረው ሰው ማንነት ዝርዝር መግለፅና የፖስፖርቱን ኮፒ የማቅረብ ግዴታ አለበት።

 

፲፮. ድንገተኛ ፍተሻ

ፖሊስ የሽብርተኝነት ድርጊት ሊፈፀም እንደሚችል በቂ ጥርጣሬ ሲኖረውና ድርጊቱን ለመከላከል ድንገተኛ ፍተሻ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን በፌዴራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር ወይም እርሱ በሚወክለው ኃላፊ ፈቃድ በአካባቢው ያለን ተሽከርካሪ እና እግረኞችን በማስቆም በማንኛውም ጊዜ በድንገት ለመፈተሽና አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ለመያዝ ይችላል።

 

፲፯. በድብቅ የሚደረግ ብርበራ

ፖሊስ፤

፩. የሽብር ድርጊት የተፈፀመ እንደሆነ ወይም ሊፈጸም እንደሚችል ፣ ወይም

፪. በሚበረብረው ቤት ውስጥ ነዋሪ ወይም ባለይዞታ የሆነው ሰው የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈፀም ዝግጅት ስለማድረጉ ወይም ዕቅድ ስለመንደፉ፣ እና

፫. የሚደረገው ብርበራ የሽብርተኝነት ድርጊት ወይም በሽብርተኝነት ድርጊት የሚጠረጠር እንቅስቃሴን አስቀድሞ ለመከላከል ወይም እርምጃ ለመውሰድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው፣

በበቂ ምክንያት ያመነ ከሆነ በድብቅ የሚደረግ የብርበራ ማዘዣ ከፍርድ ቤት እንዲሰጠው በፅኁፍ ወይም አስቸኳይ ሁኔታ ሲኖር በስልክ ፈቃድ ሊጠይቅ ይችላል።

 

፲፷. በድብቅ የሚደረግ ብርበራ ለማካሄድ ስለሚሰጥ ትዕዛዝ

፩. ፍርድ ቤቱ በአመልካች በሚቀርብለት መረጃ መሰረት፣

ሀ. የተፈፀመውን ወይም የተተረጠውን የሽብር ድርጊት ባህሪ ወይም አደገኛነት፣ እና

ለ. በማዘዣው መሰረት የሚወሰደው እርምጃ የሽብር ድርጊቱን ለመከላከል ወይም ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚኖረውን አስተዋፅኦ፤

ከግምት ውስጥ በማስገባት በድብቅ የሚደረግ ብርበራ ማዘዣ ይሰጣል።

፪. በዚህ አንቀጽ መሰረት የሚሰጥ ማዘዣ፡-

ሀ. ማዘዣው የሚመለከተውን ቤት አድራሻና የሚታወቅ ከሆነ የቤቱን ነዋሪዎች ስም፣

ለ. ከፍተኛው ሠላሳ ቀናትመሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ማዘዣው ተፈፃሚ የሚሆንበትን ጊዜና ማዘዣው የተሰጠበትን ቀን፣ እና

ሐ. እንደ አስፈላጊነቱ የሚበረበሩትንና የሚያዙትን ማስረጃዎች አይነት ወይም ዝርዝር፣

መያዝ አለበት።

 

፲፱. የመያዝ ሥልጣን

፩. በዚህ አዋጅ የተመለከተ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈፀሙ ወይም እየፈፀመ ያለ ስለመሆኑ በሚገባ የሚጠረጥረውን ማንኛውንም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፖሊስ ለመያዝ ይችላል።

፪. የተያዘው ሰው በ፵፷ ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አለው። ይህም ጊዜ ከተያዘበት ቦታ ወደ ፍርድ ቤት ለመድረስ አግባብ ባለው ግምት የሚጠይቀውን ጊዜ አይጨምርም።

 

፳. በእስር የማቆያ ትዕዛዝ

፩. በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፲፱ በተመለከተው መሠረት የተያዘ ሰው የቀረበለት ፍርድ ቤት ለምርመራ ወይም ክሱን በፍርድ ቤት ለማሰማት የተያዘው ሰው በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ሊወሰን ይችላል።

፪. ምርመራው ያልተጠናቀቀ እንደሆነ መርማሪው ፖሊስ ምርመራውን የሚፈፅምበት በቂ ጊዜ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን መጠየቅ ይችላል።

፫. በማረፊያ ቤት ለምርመራ ለማቆየት የሚሰጠው እያንዳንዱ ጊዜ ቢያንስ ለ፳፷ ቀናት ይሆናል፤ ሆኖም በአጠቃላይ የሚሰጠው ጊዜ ከአራት ወራት መብለጥ አይኖርበትም።

፬. በዋስትና ጉዳዮች ላይ ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ለማቅረብ ይችላል።

፭. በዚህ አዋጅ መሰረት በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ የቀረበ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ክሱን ሰምቶ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ተከሳሹ በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ያዛል።

 

፳፩. ናሙናዎችን የመስጠት ግዴታ

ፖሊስ በሽብርተኝነት ወንጀል ጉዳይ የተጠረጠረ ሰው የእጅ ጽሁፉን፣ የጣት አሻራውን፣ ፎቶግራፉን፣ የፀጉሩን፣ የድምፁን፣ የደሙን፣ የምራቁንና ሌሎች በሰውነቱ የሚገኙ ፈሳሽ ነገሮችን ናሙናዎች ለምርመራ እንዲሰጥ ሊያዝ ይችላል። በተጨማሪም የህክምና ምርመራ እንዲያደርግ ሊያዝ ይችላል። ተጠርጣሪው ለምርመራው ፈቃደኛ ካልሆነ ፖሊስ አስፈላጊ የሆነ ተመጣጣኝ ሀይል ተጠቅሞ ከተጠርጣሪው ናሙና ሊወስድ ይችላል።

 

፳፪. መረጃ የመስጠት ግዴታ

የሽብርተኝነት ወንጀል ለመከላከል ወይም ምርመራ ለማከናወን ፖሊስ ለምርመራው የሚረዳው መሆኑን በሚገባ የሚያምንበትን መረጃ ወይም ማስረጃ ከማናቸውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ ባለሥልጣን፣ ባክ፣ የግል ድርጅት ወይም ግለሰብ እንዲሰጠው ሊጠይቅ ይችላል። መረጃ ወይም ማስረጃ የተጠየቀው ወገን መረጃውን ወይም ማስረጃውን የመስጠት ግዴታ አለበት።

 

ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ (ኖክ) እ.ኤ.አ 2004 ዓ.ም ከተመሰረተ ጀምሮ ከአውሮፕላን ነዳጅ ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ የ250 ሚሊየን ብር ኢንቨስትመንት በማድረግ የኢትጵያ አየር መንገድን የነዳጅ ፍጆታ 50 በመቶ ድርሻ ለመውሰድ መብቃቱን ገለፀ።

 

ይህ የተገለፀው የኩባንያው የአቪዬሽን ዴፖ ማስፋፊ ያግንባታን እና ዘመናዊ የወቅቱን ከፍተኛ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተፈበረኩትን የአይሮፕላን ነዳጅ መሙያ ሪፊዩለሮች አቀባበል አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በተዘጋጀ ሥነ-ሥርዓት ላይ ነው።


የአየር መንገዱን ዕድገት አስከትሎ የኩባንያውን የቦሌ ዲፖ መሰረተ ልማት ማሳደጉ ግድ ሆኖ መገኘቱ ስለታመነበት ለአይሮፕላን ነዳጅ መሙያ ሪፊዩለሮች ግዢ እና የዴፖውን ነዳጅ ማከማቻ የማራገፊያና የመጫኛ መሰረተ ልማት ማስፋፋት ስራ እንዲከናወን የኩባንያው የቦርድ ሊቀመንበር የክብር ዶ/ር ሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል-አሙዲ በድምሩ ብር 119 ሚለዮን በጀት ፈቅደዋል።


የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኳንግቱትላም፣ በወቅቱ እንደተናገሩት የሀገሪቱ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ከአገሪቱ አጠቃላይ እድገት ጋር ተያይዞ እያደገ ነው። ከዚህ አንፃር ኖክ በነዳጅ አቅርቦትና በአጠቃላይ ለዘርፉ እድገት እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ የሚበረታታ ነው ብለዋል።


የኖክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ጥላሁን እንደገለፁት ኩባንያው ነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች ሥርጭት ሥራ ከጀመረ አስራ ሶስት ዓመትን አስቆጥሯል። በአሁኑ ሰዓትም በ180 ማደያዎች የነዳጅ ሥርጭት ሥራው በመላው ኢትዮጵያ በተቀላጠፈ ሁኔታ ተደራሽነቱ እንዲጨምር በማድረግ የገበያ መሪነቱን ተጎናጽፏል።


በቀጥታ ደንበኞችም በአገሪቱ እየተካሄድ ባሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ዋነኛ የነዳጅ አቅራቢ በመሆን ለዕድገትና ትራንስፎሜሽን እቅዱ መሳካት በኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።


የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም በታዳጊ አገሮች ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ ይገኛል። የዓለም አቀፍ ሲቪልአቪዬሽንስ ድርጅት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት እ.ኤ.አ በ2016 ወደ 3 ነጥብ 7 ቢሊየን መንገደኞች የተስተናገዱ ሲሆን ይህ አኃዝ ከ15 ዓመት በኋላ ከእጥፍ በላይ እንደሚያድግ ይጠበቃል።


በዓለም ከፍተኛውን የመንገደኞች ትራፊክ በማስተናገድ አትላንታ.፣ ቤጅንግና ለንደን 95 ሚሊየን፣ 82 ሚሊየን እና 70 ሚሊየን መንገደኞችን በማስተናገድ በቅደም ተከተል ይጠቀሳሉ።


በአፍሪካ ደረጃ ሲታይ ደግሞ ጆሀንስበርግ (O. R. Tambo International) ካይሮ (Cairo) እና ኬፖታውን (Cape Town) 20 ነጥብ 7 ሚሊዮን፣ 16 ነጥብ 5 ሚሊየን እና 10 ሚሊየን መንገደኞችን በማስተናገድ ከ1ኛ እስከ 3ኛ በደረጃ ይከታተላሉ። የአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርትም 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን መንገደኞች በማጓጓዝ በ4ኛ ደረጃ ይገኛል። ወደፊትም በአጭር ጊዜ ከላይ የተጠቀሱት የአፍሪካ ኤርፖርቶች ደረጃ ይደርሳል ወይንም ይበልጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ታደሰ ጠቁመዋል።


በዓለማች በአሁኑ ጊዜ የቀኑ የሁሉም የነዳጅ ፍጆታ 14 ሚሊየን MC እንደሆነ ይገመታል። ከዚህም ለትራንስፖርት 8 ሚሊየን MC በቀን ሲገመት ለአቪየሽን ትራንስፖርት ደግሞ የሚውለው 1 ሚሊየን MC ነው። የአፍሪካ አቪዬሽን ነዳጅ በቀን 31 ሺህ 800 MC ሲገመት ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ድርሻ በቀን 2 ሺህ 200 MC ይሆናል።


ባለፉት አስርት አመታት የአቪዬሽን ነዳጅ ፍጆታ በአለም አቀፍ ደረጃ በአማካይ በዓመት 1 በመቶ ሲያድግ በታዳጊ አገሮች ግን በአማካይ በ5 በመቶ አድጓል። ከፍተኛ እድገት ካሳዩት ውስጥ ቻይናና ሕንድ የሚጠቀሱ ናቸው።


የኢትዮጵያ የጄት ፊዩል ፍጆታ ከነበረበት በጣም አነስተኛ ደረጃ ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ከሶስት እጥፍ አካባቢ አድጓል። እ.ኤ.አ በ2004 የነበረው ፍጆታ 128,000 MC በአመት ሲሆን፣ በ2016 (እ.ኤ.አ.) 687,000 MC ደርሷል። በሚቀጥሉት አስር አመታትም ይህ አሃዝ እንደዚሁ በሶስት እጥፍ በላይ እንደሚያድግ ይገመታል።


ኖክ አቪዬሽንም ይህን ፈጣን እድገት በመገንዘብ በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ በተከታታይ እድገት በማሳየት ከ15 በመቶ፣ 21 በመቶ፣ 29 በመቶ፣ 31 በመቶ እና 38 በመቶ የገበያውን ድርሻ በመውሰድ በእ.ኤ.አ 2017 ብቻ 254 ሚሊየን ሊትር ለአውሮ ፕላኖች ነዳጅ አቅርቧል።


የአዲስ አበባ ኤርፖርትን የምስራቅ አፍሪካ ሀብ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ በተከታታይ ኢንቨስት በማድረግ የሚጠበቅበትን አገልግሎት የአለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለሟሟላት ከመቼውም በላይ በትጋት እየሰራ ይገኛል።


የነዳጁን ጥራት ለማስጠበቅ ኩባንያው በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያና የመቆጣጠሪያ ሲስተም በቅድሚያ የአይሮፕላን ነዳጅ በተወሰኑ አመላላሽ ቦቴዎች ላይ በሥራ ላይ አውሏል። ይህ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያና የመቆጣጠሪያ ሲስተም ነዳጅ አመላላሽ ቦቴዎች ላይ ማናቸውንም ህገወጥ የነዳጅ ማቀናነስም ሆነ የመቀየጥ ተግባር በሚፈፀምበት ወቅት ወዲያወኑ ወደ ተመረጡ የመከታተያና የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች በአንድ ጊዜ ሪፖርት በማሰራጨት አስፈላጊና ህጋዊ እርምጃዎች በአጥፊዎች ላይ እንዲወሰድ የሚያስችል መሳሪያ ነው።


ይህን ሲስተም በመጀመሪያ ደረጃ በአይሮፕላን ነዳጅ አመላላሽ ተሸከርካሪዎች ላይ እንዲጀመር ያስፈለገበት ዋና ምክንያት የአየር ትርንስፖርት ዘርፍ በአንፃራዊነት ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ ዓለም አቀፍ የደህንነት ህግጋትንና የአሰራርን ደረጃን የሚጠይቅ በመሆኑ ይህንኑ ለማስፈፀም በእጅጉ እንደሚረዳ በመታመኑ ነው። አስካሁን ባለው አፈፃፃም ውጤቱም እጅግ አመርቂ ሆኖ ተገኝቷል።


አዲስ የተገዙት ሪፊዩለሮች እያንዳንዳቸው 44 ሺህ ሊትር የመያዝ አቅም ያላቸውና እንዲሁም በደቂቃ እስከ 2 ሺህ 200 ሊትር ድረስ የመሙላት አቅም ያላቸው ሲሆኑ፣ የነዳጁን ጥራት በከፍተኛ ደረጃ ለመጠበቅ የሚያስችል ማጣሪያ (Filtration System) እና የናሙና መፈተሻ ተገጥሞላቸዋል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የዲፊውሊንግ (Defueling) ሥራም እንዲያከናውኑ ተገቢው መሣሪያ የተገጠመላቸው ናቸው።


እንደ አቶ ጥላሁን ገለፃ ከሆነ እያንዳንዱ ሪፊዩለር የአይሮፕላን ነዳጅ መሙያ የየራሳቸው ሊፍት (Elevating Plat form) ያላቸው ሲሆን አየር መንገዱ የሚያስመጣቸውን እጅግ ዘመናዊ አይሮፕላኖች ጭምር ለመሙላት እንዲችሉ የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተፈበረኩ ናቸው። በዚህም ሂደት 44ሺ ሊትር ለመውሰድ የሚለውን የአይሮፕላን በ20 ደቂቃ ማስተናገድ እንችላለን።


የነዚህ ዘመናዊ መሳሪያዎች ወደ ኖክ አቪዬሽን ዴፖ መካተት የኖክን የአይሮፕላን ነዳጅ የመሙላት አቅም በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ የአየር መንገዱን ፍጆታ 50 በመቶ ድረስ ለመሙላት በሚያስችለቸው ሁኔታ ላይ ያደርሱታል።
እያንዳንዱ ሪፊዩለር የ20 ሚሊዮን ብር ዋጋ ሲኖረው ሁለቱ ሪፊዩለሮች በአጠቃላይ 40 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎባቸዋል። ይህም እስከ አሁን ድረስ በአቪዬሽን ሥራ ላይ የተደረገውን የኢንቨስትመንት መጠን ወደ 250 ሚሊየን ብር ያደርሰዋል።


በአጠቃላይ የኖክ ኢንቨስትመንት በኢንዱስትሪው ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ 2 ቢሊየን ብር ሲሆን የድርጅቱ ጠቅላላ ንብረት 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ደርሷል። 

Page 1 of 15

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us