የአጠቃላይ የብቃት ምዘና ፈተና አካሄድን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ሃሳቦችን ማንሸራሸር እጅግ ይጠቅማል

Wednesday, 03 January 2018 16:11

የአጠቃላይ የብቃት ምዘና ፈተና አካሄድን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ሃሳቦችን ማንሸራሸር እጅግ ይጠቅማል 

ዶ/ር አረጋ ይርዳው

 

የትምህርት ሚኒስቴር በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም የመጨረሻ ሳምንት በተለይ ለሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች ባስተላለፈው ሰርኩላር ደብዳቤ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የቅድመ ምረቃ የትምህርት መርሃግብር ማጠናቀቂያ ላይ የአጠቃላይ የብቃት መለኪያ ወይንም የመውጫ ፈተና እንዲሰጥ አዟል። ቀደምሲል ይህ መርሃ ግብር በህግ እና በሕክምና ተማሪዎች ላይ ተግባራዊ መደረጉም የሚታወስ ነው። ይህንኑ መመሪያ መነሻ በማድረግ ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር እና የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት አነጋግረናቸዋል። ዶ/ር አረጋ ቀደም ሲል ለስምንት ዓመታት ያህል የግል የከፍተኛ ትምህርት እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ማኅበርን በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ እንደመሆናቸው መጠን መመሪያው ከግሉ ዘርፍ አንፃርም እንዴት እንደሚታይ ሃሳባቸውን ገልፀዋል። መልካም ንባብ!

 

ሰንደቅ፡- የትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና አስመልክቶ ያወጣውን መመሪያ በአጠቃላይ እንዴት አገኙት?


ዶ/ር አረጋ፡- መመሪያውን አንድ ቦታ ላይ አግኝቼ እንደተመለከትኩት ጥቅምት 21 ቀን 2010 ዓ.ም ከትምህርት ሚኒስቴር የወጣ ነው። ደብዳቤው በቀጥታ የተፃፈው ደግሞ ለመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች ብቻ ነው። የግል ዩኒቨርሲቲዎችንና ኮሌጆችን አላካተተም። ይህ ለምን እንደሆነ በግሌ አላወኩም። ምናልባት ተመሳሳይ ደብዳቤ ለግል ትምህርት ተቋማትም ተፅፎ ነገር ግን ሳልመለከተው ቀርቼ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የሚመለከት መመሪያ ግን ወጥ በሆነ መልኩ በመንግሥትም በግልም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተግባራዊ ቢሆን ጠቀሜታው የበለጠ ከፍ ያለነው። የትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በቅድመ ምረቃ ትምህርት መርሃ ግብር ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና እንደሚወስዱ ይገልፃል። ይህን ፈተና አንዳንዶቹ የመውጫ ፈተና ይሉታል፣ ሌሎቹ አጠቃላይ ምዘና ወይም የብቃት መለኪያ በማለት ይጠሩታል። አጠራሩ በራሱ ትንሽ ደብለቅለቅ ያለ ይመስላል። በትርጉም ደረጃ ግን አንዱ ከአንዱ ልዩነት አለው። ለአሁኑ ቃለመጠይቅ አጠቃላይ የምዘና ፈተና የሚለውን ወስደን መነጋገር እንችላለን። በመመሪያው መሠረት ፈተናው ተግባራዊ የሚሆነው ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ነው። እንግዲህ መመሪያው በ2011 ዓ.ም የሚተገበር ከሆነ ወደኃላ ተመልሶ በ2009 ዓ.ም ትምህርት የጀመሩ ተማሪዎችን የሚመለከት ይሆናል ማለት ነው። ይህ ስሌት እንግዲህ አንድ ተማሪ ዲግሪውን ለመውሰድ ሶስት ዓመት ሊፈጅበት ይችላል በሚል ያስቀመጥኩት መሆኑ ይታወቅ። መመሪያው ወደኋላ ሄዶ፣ ስለፈተናው ምንም መረጃ ያልነበራቸው ተማሪዎች ፈተና እንዲቀመጡ ያስገድዳል ማለት ነው። ይሄ በራሱ ችግር አለው ብዬ አስባለሁ። ፈተናው የግድ አስፈላጊ ከሆነ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከሚገቡ አዲስ ተማሪዎች ጀምሮ ሥራ መሠራት አለበት። በሂደት ላይ ያሉትን ተማሪዎች መካከል ላይ ተገብቶ እንዲህ ዓይነት ፈተና ውሰዱ ማለት ችግር ሊኖረው ይችላል። አንዳንድ ሰዎች ለፈተና ዝግጅት አያስፈልግም፣ ያለውን ነገር ነው የምንፈትነው ሊሉ ይችላሉ። በእኔ ዕይታ ፈተና አለ ብሎ መዘጋጀትና በድንገት መፈተን አንድ ናቸው ብዬ አላስብም።
ሌላው ዓቢይ ጉዳይ ግልፅነት ያስፈልገዋል ብዬ የማስበው ይሄ አጠቃላይ ፈተና ዲግሪን ለማግኘት እንደአንድ መመዘኛ (Requirement) ከሆነ ካሪኩለም ውስጥ መካተት አለበት። ክሬዲት ሰዓትም (hours) መታወቅ አለበት። ይሄ ከአሁን በፊት በሙከራ ላይ በነበሩት እንደ ሕግ እና ህክምና የትምህርት ዓይነቶች ላይ ተግባራዊ የሆነ ነው። አንድ ተማሪ ዲግሪ ለማግኘት የሚያስፈልገው አጠቃላይ ክሬዲት ሰዓት ይታወቃል። የመውጫ ፈተናውም ክሬዲት ሰዓት ተሰጥቶት ተምሮ ለፈተና መቅረብ አለበት። ካሪኩለሙም የአጠቃላይ የምዘና ፈተናውን ያካትታል ተብሎ መቀመጥ አለበት። አጠቃላይ የምዘና ፈተናው በካሪኩለም ከተቀረፀ መምህራን ያውቁታል፣ የዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች የአስተዳደር ሠራተኞች ያውቁታል፣ ለፈተናውም በቂ ዝግጅት ለማድረግ ይረዳል። መጨረሻ ላይ ውጤቱም ያማረ ሊሆን ይችላል።

 

ሰንደቅ፡- የአጠቃላይ ምዘና ፈተና በአንድ የሙያ ዘርፍ ተጨማሪ ብቃትን ከሚያስገኙ ፈተናዎች ይለያል?


ዶ/ር አረጋ፡- ፕሮፌሽናል ኤግዛሚኔሽን የሚባሉ አሉ። ለምሳሌ መሐንዲሶች የብቃት ፈተና ወስደው ፕሮፌሽናል መሐንዲሶች ይሆናሉ። አካውንታንቶች ፈተና ወስደው የተመሰከረላቸው የሂሳብ አዋቂ የሚል ሠርተፊኬት ያገኛሉ። የጤና ባሙያዎችም እንዲሁ ሠርቲፋይድ የሆኑ ባለሙያዎች ይሆናሉ። ሌላው እንዲሁ። ይሄ ሁሉም ባለሙያ ከዩኒቨርስቲ ተመርቆ ከወጣ በኋላ በራሱ ጥረት የሚያገኘውና አንዱ ከሌላው የሚለይበት ይመስለኛል። ይሄ ሊደገፍና ሊበረታታ ይገባል። የአጠቃላይ ምዘናው ግን አንድ ተማሪ በትምህርት ገበታው ላይ በቆየባቸው ጊዜያት ያገኛቸውን መሠረታዊ እውቀት ለመለካት የሚያገለግል ነው ስለተባለ የዲግሪው አካል ነው ማለት ነው።

 

ሰንደቅ፡- የአጠቃላይ ምዘና ፈተና መኖር ከትምህርት ጥራት መሻሻል ጋር የሚያያይዘው ነገር ይኖረዋል?


ዶ/ር አረጋ፡- ጥራት (ኳሊቲ) በአሁኑ ጊዜ ዲዛይን ላይ ያለ ነገር ነው። ውጤት (Result) ብቻ በመለካት ኳሊቲን ማረጋገጥ አይቻልም። ግብአት (Input) እና ሒደት (Process) ለትምህርት ጥራት መገኘት ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው። የመማር ማስተማር ላይ ያለው ሒደት በጥራት የተሟላ ሲሆን ውጤቱ ጥራት ያለው ይሆናል። ስለዚህ ጥራት ያለው ውጤት የግብዓትና የሂደት (Process) ድምር ውጤት ስለሆነ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል።


ፈተና አንዱን ከሌላው ለመለየት አስፈላጊ ስለሆነ የሚሰጥ ነው። ለምሳሌ የባችለር ዲግሪ ይዘህ ማስተርስ ዲግሪ ለመማር ብትፈልግ አንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመግቢያ ፈተና ይሰጣሉ። ተማሪው ለሚሳተፍባቸው የትምህርት ዓይነቶች ተገቢው መሠረት ያለው መሆኑን ለማረጋገጥ ነው። ስለዚህ ለመለየት እንዲመቻቸው ፈተና ይሰጣሉ። የተማሪውን የእውቀት ደረጃ የቱን ያህል እንደሆነ ማወቅ ጥቅም ስላለው ነው። አሁን በትምህርት ሚኒስቴር አዲስ መመሪያ መሠረት በየትኛውም በቅድመ ምረቃ የትምህርት መስክ ዲግሪ ለማግኘት አጠቃላይ የምዘና ፈተና ውሰዱ መባሉ አስቀድሞ የታወቀ ከሆነ፣ የካሪኩለም አካል ከሆነ፣ ቀደም ያለ ዝግጅት የተደረገበት ከሆነ የሚከፋ አይደለም። ከሁሉ በላይ ግንዛቤ የሚያሻው ለፈተና የቀረቡ ወጣቶች ፈተናውን ማለፍ ባይችሉ ምንድነው የሚደረገው፣ መታወቅ አለበት ቅድመ ዝግጅትም ያስፈልገዋል። ምክንያቱም ሶስት ዓመት የለፋን ወጣት ፈተና ባያልፍ በምን ዓይነት መልክ ነው መቀጠል የሚችለው። አንድ ቦታ 100ሺህ ተማሪዎች ለፈተና ቢቀርቡና የተወሰኑት ፈተና ላይ እንከን ቢኖራቸው ምንድነው የሚሆነው የሚለውን መመልከትና ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል። እንዲህ ዓይነት ክፍተቶች ቀላል ቢመስሉም ከባድ የማህበረሰብአዊ ዋጋ የሚያስከፍሉ መሆናቸው መታወቅ አለበት። አጠቃላይ ምዘና በጣም የሚፈለግባቸው የትምህርት መስኮች እንዳሉ አውቃለሁ። ለምሳሌ ጤና ላይ ተደርጓል፤ አስፈላጊ ነው። ይህን ማጠናከር ይገባል። በሁሉም የትምህርት መስኮች ላይ ምዘና ማድረግ አስፈላጊ ነው ወይ የሚለው በጥሞና መታየት አለበት።


እኔ የምደግፈው አካሄድ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲኖር ሥራዎች መከናወን ያለባቸው ከሥር ጀምሮ ነው። ከሥር በቂ ሥራ ከተሠራ ተማሪዎቹ ወደከፍተኛ ትምህርት ሲሸጋገሩም ፈተና ኖረም፣ አልኖረም የብቃት ሆኖም የጥራት ጉዳይ ጥያቄ የሚነሳበት አይሆንም።

 

ሰንደቅ፡- የመውጫ ፈተና ወስዶ ማለፍ ብቻውን የተማሪውን ብቃት ለመመስከር በቂ ነው ይላሉ?


ዶ/ር አረጋ፡- ፈተና መውሰድ ብቃትን ለማረጋገጥ በቂ መሣሪያ ነው ብለው የሚያምኑ ወገኖች አሉ። በተቃራኒው በቂ አይደለም ብለው የሚያምኑም አሉ። እኔ ፈተና አስፈላጊ ነው ሆኖም ብቻውን በቂ መለኪያ አይደለም ከሚሉት ወገን ነኝ። አንድ ሰው ከተማረ በየቀኑ በሚያሳየው መሻሻል ውጤቱን መለካት ይቻላል። ምን ያህል ጠንካራ ወይም ደካማ እንደሆነ ማወቅ ይቻላል። አንድ ተማሪ ምን ዓይነት ዕውቀት ጨብጧል ብሎ ለመመዘን የዚህ ዓይነት ፈተና ቢሰጥ ነውር የለውም። መጨረሻ ላይ በሚሰጥ ፈተና ብቻ ግን ጥራት ተረጋግጧል፣ አልተረጋገጠም ለማለት ግን አስቸጋሪ ይሆናል። ጥራት ሒደት ላይ ነው ማተኮር ያለበት። ሒደቱ (Input እና Process) ላይ የተጠናከረ ሥራ ከተሠራ ውጤቱ ጥሩ እንደሚሆን ግልፅ ነው። በቅርብ የተከፈቱ ዩኒቨርስቲዎች አሉ። ሀገራችን ባለፉት ዓመታት ከነበራት ሁለት የመንግሥት ዩኒቨርስቲ ከ40 በላይ ደርሰዋል። የግል ዘርፉ ላይ ከ100 በላይ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች አሉ። የተማሪዎች ቁጥር እጅግ ብዙ ነው። ስለሆነም ያለን የሰው ኃይል አሟጦ ለመጠቀም ፈተና የሚያልፍም የማያልፍም ለማህበረሰቡ አስተዋጽኦ የሚያደረጉበት ስትራቴጂ ከፈተናው ጋር አብሮ መታየት አለበት።

ሰንደቅ፡- የመውጫ ፈተና በቅድመ ምረቃ ሁሉም የትምህርት ዘርፎች ላይ ተግባራዊ እንዲሆን ከመወሰን ይልቅ ቀደም ሲል በሕግና በሕክምና ትምህርት መስኮች እንደተጀመረው ዓይነት በተመረጡ የትምህርት መስኮች ጀምሮ ቀስ በቀስ እያስፋፉ መሄዱ ይበልጥ ተመራጭ አይመስልዎትም?


ዶ/ር አረጋ፡- ይህ አንድ መንገድ ነው። በተመረጡ የትምህርት መስኮች ብቻ አተኩሮ እያሰፉ መሄድ የበለጠ ተመራጭ ሊሆን እንደሚችል የእኔም ሃሳብ ነው። ትምህርት ሚኒስቴርም በጤና እና በህግ ያለውን ተሞክሮ ወስዷል ብዬ አምናለሁ። ሆኖም ለሁሉም የትምህርት መስኮች የመውጫ ፈተና ማድረግ ተገቢና አስፈላጊ ነው ወይ የሚለው በጥሞና መታየት አለበት። ለምሳሌ ያህል እጅግ በጣም የተሟላ የመማር ማስተማር ተግባርን ከሚያከናውኑት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል መርጦ ‹‹በፈቃደኝነት›› የመመዘኛ ፈተና በመስጠት ውጤቱን መርምሮ ጉድለቱን አስተካክሎ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች መተግበር የተሻለ አካሄድ ሊሆን ይችላል። ከዚሁ ጋር አብሮ መታየት ያለበት መመሪያው ከመውጣቱ በፊት በቂ ውይይት፣ ምክክር ከባለድርሻ አካላት ጋር ተደርጓል ወይ ብሎ መጠየቅም ያስፈልጋል። እኔ አስከማውቀው ድረስ በግል የትምህርት ተቋማት አልተደረገም። ይህ መመሪያ ራሱ ለግሉ ዘርፍ የደረሰ አይመስለኝም።

 

ሰንደቅ፡- በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበር ፕሬዚዳንት ሆነው እንደማገልገልዎ ቀደም ሲል በሕግ እና በህክምና የትምህርት ዘርፎች ሙከራ ላይ የነበረው የመውጫ ፈተና ውጤታማ ነበር ያላሉ?


ዶ/ር አረጋ፡- በ2002 ዓ.ም ይመስለኛል፤ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጥራት ላይ ችግር አለባቸው በሚል፣ እንዲያውም መዘጋት አለባቸው የሚል የውሳኔ ሃሳብ መጥቶብን እንደነበር አስታውሳለሁ። ከዚያ በኋላ ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን የትምህርት ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በጉዳዩ ላይ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ሰፊ ውይይት ተቋማቱን ከመዝጋት ይልቅ ማስተካከል ያለባቸውን ነገሮች ያስተካክሉ የሚል ውሳኔ ላይ ተደረሰ። በወቅቱ የሕግ እና የመምህራን ማሰልጠን በግል ዘርፍ እንዳይሰጥ የሚል ውሳኔም መተላለፉን አስታውሳለሁ። ሆኖም ግን እኔ እስከማውቀው ድረስ በፅሁፍ የተሰጠ ውሳኔ መኖሩን አላስታውስም። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሕግ እና መምህራን ማሰልጠን በግሉ ዘርፍ እንዲቆም ሆነ። በዚያን ወቅት ቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ መምህራንን በማሰልጠን በጣም የታወቀ ነበር። ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ደግሞ በሕግ የትምህርት ዘርፍ በጣም የታወቀ ነበር። በወቅቱ ለዩኒቲ ዩኒቨርስቲ የሕግ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ተሰጥቷቸው በሚያስደንቅ ሁኔታ እንዳለፉም አስታውሳለሁ።


በወቅቱ የታገዱት የሕግ እና የመምህራን ማሰልጠን ጉዳይ ለምን እስካሁን እንደታገዱ እንደቆዩ ወይም እንዳልተፈቀደ አላውቅም። ምናልባት ስላልጠየቅን ሊሆን ይችላል። በሀገር አቀፍ ደረጃ የመምህራን እጥረት እያስቸገረን ባለበት በዚህ ጊዜ የግል ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች መምህራንን ማሰልጠን ቢያደርጉ ጥቅም ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ። በህግ ትምህርት በጣም የተደራጁና ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው እንደዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ያሉት እንዲሰጡ ቢደረግ እንደሀገርም ጠቀሜታ ስላለው የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን ደግመው እንዲያጤኑት ማሳሰብ እወዳለሁ። መንግስት በህግና በመምህራን ማስተማር ላይ ለወሰደው ውሳኔ የራሱ ምክንያት ካለው በትምህርት ዘርፉ ያለን ባለድርሻ አካላት እንድንረዳው ቢያደርግ ጥሩ ይመስለኛል። የግሉ ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪ ፕሮግራም ለማስፋፋት፣ የፒኤችዲ ፕሮግራም ለመጀመር ቢፈልግ እንኳን በቂ የሆኑ መምህራን የሉንም። ስለዚህ በግሉ ዘርፍ መምህራን ቢሰለጥኑ ከጠቅላላው የዲግሪ ተማሪዎች 15 በመቶ የያዘው የግል የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ በይበልጥ ተጠናክሮ አወንታዊ አስተዋጽኦ ሊያደረግ ይችላል። የአጠቃላይ የብቃት ፈተና አካሄድን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ሃሳቦችን ማንሸራሸር እጅግ ይጠቅማል።

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
304 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 830 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us